AMN- መጋቢት 8/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ከመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ጋር በጋራ በሰራው ስራ ከ71 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በመንግስት ተቋማት ያሉ ብልሽት የገጠማቸው የቴክኖሎጂ እቃዎች እንዲሁም የኤሌትሮኒክስ ቁሶችን ጠግኖ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ነው ገንዘቡን ማዳን የተቻለው።
በዚህም የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት የሚያጠናክር ሙያዊ ስራ ማከናወኑ የተገለጸ ሲሆን በሌላ በኩል የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ስለመቻሉም ተመላክቷል።
በጋራ በተሰራው ስራ ከዳነው 71 ሚሊየን ብር ውስጥ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው የጥገና አገልግሎት ለሚሠጡ ባለሙያዎች የሚከፈል የነበረ ወጪ መሆኑ ተመላክቷል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ይህንኑ ተግባር ለማጠናከር በቀጣይ ለጥገና አገልግሎት አጋዥ የሆኑ የተለያዩ የጥገና ቁሳቁሶችንም ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች ድጋፍ አድርጓል::
በአንዋር አህመድ