በመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረገ

You are currently viewing በመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረገ

AMN – ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ያሉበት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርጓል።

የልዑካን ቡድኑ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ ማህሙድ ጋር ውጤታማ ውይይት ያደረገ ሲሆን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ለፕሬዚዳንቱ የተላከ መልዕክት አድርሰዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሶማሊያ እና በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የAUSSOM ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመስራት የተስማሙ ሲሆን የሁለትዮሽ ትብብራቸውንም ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የጉብኝት ልውውጦች ለማጠናከርና በቅርቡ የሶማሊያ ከፍተኛ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ጉብኝት በማድረግ ውይይት ለማካሄድ ተስማምተዋል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብድርቋድር ኑር ጃማ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሶማሊያን ሰላም ለማረጋገጥ ለከፈለው መስዋትነት እና ላበረከተው አስተዋጽዖ ያላቸውን አክብሮት እና ምስጋና ገልጸዋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መከላከያ ሚኒሰትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያላት ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ ሽብርተኝነትን መዋጋት የሁለቱ አገራት ቁልፍ የትብብር ማዕከል መሆን እንደሚገባው አስምረውበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው የሶማሊያ ሰላም ማለት የኢትዮጵያ ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣናው የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር አገራቱ የልማት አጀናዳዎቻቸው ላይ እንዳያተኩሩ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ሁለቱ አገራት ትብብራቸውን በማጠናከር ከጸጥታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በፍጥነት በመቅረፍ ሙሉ ትኩረትን ልማት ላይ ማደረግ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ሞሀመድ ኦማር የተመራ የሶማሊያ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ከሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር ውይይቱ ማድረጉ ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review