AMN – ጥር 16/2017 ዓ.ም
ከመደመር ተከታታይ መጻሕፍት ሽያጭ በተገኘ ገቢ 34 የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በባህል፣ በስፖርት እና በኪነ-ጥበብ ዘርፎች የከተናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መንግሥት ዘርፉ የሚመራበትን የሕግ ማዕቀፍ ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ተግባራትን በትኩረት ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ እሴቶችንና ቋንቋዎችን የማልማት እና በስፖርት ብቁና ንቁ ትውልድ የመፍጠር እንዲሁም አሸናፊ ሀገር የመገንባት ተልዕኮውን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከስፖርት ልማት አንጻርም በመላ ሀገሪቱ የማዘውተሪያ ስፍራዎች በስፋት መገንባታቸውን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከተጻፉት የመደመር መንገድ እና የመደመር ትውልድ መጻሕፍት የሽያጭ ገቢ ደረጃቸውን የጠበቁ 34 የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች አገልግሎት መጀመራቸውን አንስተዋል።
ይህም የታዳጊዎችን የማዘውተሪያ ስፍራ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በስፋት እየተተገበረ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የተሳታፊዎች ቁጥር ከለውጡ በፊት ከነበረበት 15 በመቶ ወደ 22 ነጥብ 7 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና በሌሎችም ትላልቅ ከተሞች ባህል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ነው ያነሱት።
በሌላ በኩል ባለፉት የለውጥ ዓመታት ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ ለማስተላለፍ ቅርሶችን የማደስ፣ የመጠገንና የማስዋብ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
ባህላዊና ኃይማኖታዊ በዓላትን እንዲሁም እሴቶችን ለማስተዋወቅና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች አመርቂ መሆናቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡