በመዲናዋ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል

You are currently viewing በመዲናዋ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል

AMN – ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ከ“ቴክኖ ሰርቭ” ጋር በመተባበር “ደረቅ ቆሻሻ ሀብት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀን የሚቆይ አውደ ርዕይ በጊዮን ሆቴል ተከፍቷል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፣ በዘርፉ ከ3 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ከተማዋ ከምታመነጨው ደረቅ ቆሻሻ የሚገኘውን ገቢ ከ 6 በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።

ቆሻሻ ሀብት መሆኑን በመግለጽ ይህንን ስራ ከተማዋ አሁን ከጀመረችው የኮሪደር ልማት ጋር እያጣጣሙ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በበኩላቸው፣ ከተሞች የሚያመነጩት ቆሻሻ ላይ ከተሰራ ሀብት እንደሚሆን አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ለማ፣ በከተማዋ የሚመነጩ ደረቅ ቆሻሻዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሀብትነት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከ80 ሺህ ቶን በላይ የሚሆነውን ቆሻሻ ወደ ሀብትነት መቀየር መቻሉን ተናግረዋል።

ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድም ከ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉንም ገልጸዋል።

በከተማዋ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሀብትነት የሚቀይሩ 350 ማህበራት መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን እነዚህ ማህበራት ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን የገለጸው ደግሞ “ቴክኖ ሰርቭ” ነው።

በሄለን ጀንበሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review