በአዲስ አበባ የቋንቋ አካታችነት ጥያቄን ለመፍታት ከአማርኛ በተጨማሪ በሶስት ሀገራዊ ቋንቋዎች የመንጃ ፈቃድ ስልጠና እንዲሰጥ መፈቀዱን የከተማው አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ ከሚሰጣቸው በርካታ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ አዲስ መንጃ ፍቃድ አገልግሎት ነው።
የእጩ አሽከርካሪዎች የንድፈ ሃሳብ ስልጠና እና ፈተና በአማርኛ ቋንቋ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ ብዙዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በአማራጭነት ቢሰለጥኑ እና ቢፈተኑ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረ የመልካም አስተዳድር ጥያቄ እንደነበርም አንስቷል።
አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ቤት መሆኗን በማመንም ለመንጃ ፍቃድ ስልጠና ፍቃድ ከሰጣቸው 137 ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ከአማርኛ በተጨማሪ በሶስት ሀገራዊ ቋንቋዎች ማለትም በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ እና በሶማልኛ ቋንቋዎች ለማሰልጠን ፍቃደኛ መሆናቸውን የገለፁ እና ሞዴል ተቋማት ለሆኑ 12 ማሰልጠኛ ተቋማት ፍቃድ መስጠቱን ገልጿል።
ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርቡ ለነበሩ ዕጩ አሽከርካሪዎች ከአማርኛ በተጨማሪ በቀረቡት የቋንቋ አማራጮች መሰልጠን እና መፈተን የሚችሉ መሆኑን መግለጹን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።