![](https://www.amn.gov.et/wp-content/uploads/2025/01/473115671_1033765025463537_8544926338617094933_n.jpg)
AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ በጤናው ዘርፍ በተዘረጉ አዳዲስ አሰራሮች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፣ ቢሮው ዜጎችን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በህክምና ማዕከላት ከመግቢያው ጀምሮ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር ያነሱት ምክትል ሃላፊው፣ አሰራሩ ወደ ዲጂታል በመቀየሩ ችግሮቹ በየደረጃው መፈታት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
![](https://www.amn.gov.et/wp-content/uploads/2025/01/473055351_1033765022130204_1325151601647949164_n.jpg)
በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች የአገልግሎት አሰጣጡን ከካርድ ክፍል ጀምሮ የማስተካከል ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በተደጋጋሚ ይስተዋል የነበረውን የካርድ መጥፋት እና የወረፋ ችግር መቅረፍ እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር መድሃኒቶች ከገቡ በኋላ በሀሰተኛ ሰነድ ማውጣትን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ለምዝበራ ይጋለጡ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም በተዘረጋው አዲስ አሰራር፣ በመድሃኒት አቅርቦት እና ህገ-ወጥ ሽያጭ ዙሪያ ይታይ የነበረውን ክፍተት ከማስተካከል አኳያ ትልቅ መሻሻል መታየት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ተገልጋዮች በተለይም በድንገተኛ ክፍል ወረፋ በመጠበቅ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እና በተኝቶ ህክምና በአልጋ ማጣት ይፈጠር የነበረውን መጉላላት ማስተካከል እንደተቻለ ዶክተር ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡
በሆስፒታሎች እና በጤና ጣቢያዎች መካከል ትስስር በመፍጠርም ሆስፒታል መጥተው መታከም የሚገባቸው ታካሚዎች ብቻ በሆስፒታል እንዲታከሙ፣ ሌሎች ደግሞ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲያገኙ መሰራቱንም አመላክተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው