በመዲናዋ እስከ አሁን ለጨረታ የቀረቡ ቦታዎች በአግባቡ ወደ ልማት መግባታቸው ተገለፀ

You are currently viewing በመዲናዋ እስከ አሁን ለጨረታ የቀረቡ ቦታዎች በአግባቡ ወደ ልማት መግባታቸው ተገለፀ

• የ3ኛው ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ አሸናፊዎች ስም ዝርዝር ይፋ ሆኗል

በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙሮች ለጨረታ የቀረቡ ቦታዎች በአግባቡ ወደ ልማት መግባታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው የ3ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡ ተጫራቾች ስም ዝርዝርንም ይፋ አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የለማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ በተለይ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ እንደገለፁት በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየው መሬትን በሊዝ የማስተላለፍ ተግባር ዳግም ከተጀመረ ወዲህ በሊዝ የተላለፉ ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ መልማታቸውን ገልፀዋል።

ለጨረታ ቀርበው የቀሩት ቦታዎች በየዙሩ የሚካተቱና ከይገባኛል ነፃ ሆነው ከመሬት ባንክ ወጪ የሚደረጉ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ በሊዝ ጨረታ የተላለፉ ቦታዎች ለተፈለገው ዓላማ እየዋሉ ነው

እስከ አሁን በአንደኛው ዙር 14 ሄክታር፣ በሁለተኛው ዙር 12 ሄክታር እንዲሁም በሦስተኛው ዙር 7 ነጥብ 8 ሄክታር  የሚሆን ቦታ ለሊዝ ጨረታ ቀርቧል፡፡ በሦስተኛው ዙር በካሬ ሜትር የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ በአራዳ ክፍለ ከተማ ሲሆን፣ ይህም 268 ሺህ ብር ነው። ዝቅተኛው ዋጋ ደግሞ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሲሆን 15 ሺህ ብር በካሬ ሜትር ነው፡፡ በጨረታው 4 ሺህ 184 ተጫራቾች ተሳትፈዋል ብለዋል፡፡

በሊዝ ጨረታው የቀረቡት በአራዳ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ፣ በአዲስ ከተማ፣ በጉለሌ እና በልደታ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ለተለያዩ አገልግሎቶች የተዘጋጁ የልማት ቦታዎች ናቸው፡፡

ቢሮው እነዚህን ቦታዎች በጨረታ አወዳድሮ በሊዝ ለማስተላለፍ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ማውጣቱና ከሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 02 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በይፋ ተከፍቶ አሸናፊዎች መለየታቸውን አስታውቋል፡፡

ቢሮው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ እንደገለፀው፣ ስማቸው በአዲስ ልሳን ጋዜጣ በወጣው ማስታወቂያ መሰረት 1ኛ የወጡ አሸናፊ ተጫራቾች ማስታወቂያው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር (10) ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ለም ሆቴል አካባቢ ኤም.ኤ ህንጻ ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ 3ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 303 በመቅረብ የሊዝ ውል መፈፀም ይኖርባቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ አንደኛ ተጫራቾች ውል የማይፈጽሙ ከሆነ በደንቡ መሰረት ዕድሉ 2ኛ ለወጡ ተጫራቾች ይሰጣል፡፡ 2ኛ የወጡ ተጫራቾች በተመሳሳይ ውል የማይፈጽሙ ከሆነ 3ኛ የወጡ ተጫራቾች በሊዝ ደንብ 162/2016 እና በተጫራቾች መመሪያ ላይ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በውስጥ ማስታወቂያ ጥሪ እንደሚያደርግ ቢሮው አስታውቋል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review