
AMN – ግንቦት 16/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የስምምነት ፊርማውን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በጋራ አከናውነዋል።
የስራ ኃላፊዎቹ ጉዳዩን አስመልክተው በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፤ ስምምነቱ የአዲስ አበባ አተማ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ25/75 መርሃ ግብር የመንግስት ሠራተኞች የቤቶች ልማት ፕሮጀክትን በጋራ የማልማት አላማ ላይ የተመሠረተ ነው።
የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዋ እንደገለጹት የመንግስት ሠራተኛው 25 በመቶውን የቤቱን ዋጋ እንዲቆጥብና ቀሪውን 75 በመቶውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር በመገንባት ሠራተኞቹ በ20 አመት ጊዜ ውስጥ እንዲከፍሉት የሚያስችል ነው።

በመኖሪያ ቤት እጦት እየተቸገሩ የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ፕሮጀክቱ ጥያቄያቸውን የሚመልስ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሚገነቡት ቤቶች ለ41 ሺህ ገደማ የመንግስት ሠራተኞች ሲሆን የመሬት አቅርቦትና ተያያዥ ሁኔታዎች ከተቀላጠፉ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ግንባታውን እናጠናቅቃለን ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ናቸው።

የቤት ዕድሉ የቅድሚያ ተጠቃሚ ለመሆን በማህበር ተደራጅተው ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟሉት የከተማዋ መምህራን መሆናቸው በተሠጠው መግለጫ ላይ የተገለጸ ሲሆን በሂደት ሁሉም ቤት የሌላቸው የከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል መንግስት ሠራተኞች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
በምትኩ ተሾመ