AMN – የካቲት 24/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቂሊንጦ ቁጥር 2 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጂ+4 ህንፃ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፣ የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ለአብነትም ከተማሪዎች ምገባ ጀምሮ ምቹ የሆኑ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች መገንባት ግንባር ቀደም ተግባር ስለሆነ በቂልጦ የተደረገውም ማስፋፊያ የዚሁ አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ አካባቢ ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአንድ ትምህርት ቤት በሶስት ፈረቃ እንዲማሩ አስገድዶ እንደነበር ያነሱት ኃላፊው፣ ይህም በአንድ ክፍል ውስጥ ከ90 በላይ ተማሪዎች እንዲማሩ በማድረግ በትምህርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የተገነቡት ትምህርት ቤቶች ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆኑ ከዚህ በፊት የነበረውን መጨናነቅ ከመቅረፍም ባሻገር አረንጓዴ ስፍራዎችም ያሉት ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቢሮው በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑ ያነሱት ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ፣ በዚህም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ከመቀነስ ጀምሮ በርካታ ለውጦች ማምጣት ስለመቻሉ ገልጸዋል፡፡
ትውልድ ላይ መስራት ሀገርን መስራት መሆኑን የገለጹት ሀላፊው፣ ከተማ አስተዳደሩም ይህንን አፅንኦት ሰጥቶ በተለያዩ ዘርፎች ትውልድ የሚቀረፅባቸው ተቋማትን በስፍትና በጥራት እየገነባ ስለመሆኑም ጠቁመዋል
በራሄል አበበ