በመዲናዋ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing በመዲናዋ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

AMN- ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም

በመዲናዋ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመቀነስ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እና የችግሩን መንስኤዎች በመለየት ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡

ኢንጂነር ወንድሙ፣ በጉባኤው ከጎርፍ አደጋ ስጋት ጋር ተያይዘው ለተነሱ ሀሳብ እና ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ በማብራሪያቸው፣ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች፣ አስቸኳይ መፍትሔ የሚሹ እና በተደጋጋሚ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን የመለየት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችም በዘላቂነት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት አንፃር ጥናት ተጠንቶ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

በዋነኛነት የችግሩ መንስኤ የፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች በተለያየ ሁኔታ በግንባታ ተረፈ ምርቶች እና ከቤት ውስጥ በሚወጡ ቆሻሻዎች የተዘጉ በመሆናቸው ጎርፍን በተገቢው መንገድ ማስወገድ አለመቻላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ ሁለት ወራት የዝናብ ጊዜ ከመምጣቱ በፊት የፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶቹን በማጽዳት፣ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ከአንዳንዱ ቦታዎች ሰዎችን የማንሳት፣ የጎርፍ መከላከያ ግንቦችን መገንባት እና ተገቢ ማስወገጃ የመስራት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review