AMN – ህዳር 30/2017 ዓ.ም
በመጀመሪያው ዙር የመንገድ ኮሪደር መሰረተ ልማት በ 44 ቦታዎች ከ4ሺ 230 በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚይዙ የመኪና ማቆሚያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
የባለስልጣኑ የፓርኪንግ፣ የመንገድ ትራፊክ መሰረተልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ጌታቸው እንደገለጹት፣ የመኪና ማቆሚያዎቹ በአጠቃላይ 111 ሺ 685 ካሬ ሜትር በላይ ይሸፍናሉ፡፡
ቦታዎቹ አሽከርካሪዎች በቀላሉ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎችን ማግኘትና መጠቀም እንዲችሉ እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበረውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታን ለመፈለግ የሚወስደውን ውጣ ውረድ መቅረፍ የቻለ ነው ብለዋል፡፡
በመንገድ ኮሪደር መሰረተ ልማት የተገኙት እነዚህ የፓርኪንግ ቦታዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የትራፊክ እንቅስቃሴ ደህንነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ፍሰትን ለመጨመር የሚያከናውን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ በእጅጉ የሚያግዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትም የፓርኪንግ መሰረተልማት አቅርቦትን ለመጨመር እየተሰራ እንደሚገኝ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡