AMN-ጥር 4/2017 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ በመጀመሪያ ጉባኤው ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የሀገርን እድገት ወደፊት የሚያራምዱ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
ፓርቲው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከልም ዜጎችን የሚያንገላታ አገልግሎት አሰጣጥን መቀየር፣ የሀገርን የኢኮኖሚ መዛባት በማስተካከል በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ፣ ብልፅግና ፓርቲ ይዞት የተነሳውን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ዜጎችን የሚያንገላታ አገልግሎት አሰጣጥን ከመቀየር ጋር ተያይዞ በዋነኛነት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ዲጂታላይዝ በማድረግ ብሎም ተጠያቂነትን በማስፈን በአቋራጭ ለመክበር የሚሞክሩ አካላትን የመታገል ሥራ ተከናውኗል፡፡
ይህም በዋናነት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚረዳ የሪፎርም ሥራ ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
በዚህም አገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ እና ዲጂታላይዝ በማድረግ በአገልግሎት አሰጣጥ የዜጎችን እንግልት ለማስቀረት በተሠራው ሰፊ ሥራ ይበል የሚያሰኝ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያን ማዘመን ያለ ዲጂታላይዜሽን የሚረጋገጥ ባለመሆኑ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚደርገው ምርምር እና የሚፈሰው ሙዓለ ንዋይም እየጨመረ መጥቷል፡፡
የሀገርን ኢኮኖሚ ካለበት የስርዓት ስብራት የተነሳ ዜጎችን በኑሮ ውድነት እየፈተነ በመሆኑ የኢኮኖሚ መዛባቱን በማስተካከል በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡
በዚህም በ2010 ዓ.ም የተደረገውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ መንግሥት አያሌ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራትን አከናውኗል።
የዕዳ ጫና፣ ገና ብዙ ሥራ የሚፈልገው የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ዝቅተኛ የዘርፎች ምርታማነት፣ ዝቅተኛ የልማት ፕሮጀከቶች አፈጻጸም እና የሀብት ብክነት፤ የተረከባቸው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕዳዎች ነበሩ።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ብዙ የፖሊሲ ሐሳቦችን በውስጡ ያካተተ እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያሳካ ነበር።
ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም በተደረገው ጥረት ውጤቶች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳዩ ካሉ ሀገራት አንዷ ሆናለች።
በቅርቡ የጸደቀው ሁለተኛው ታሪካዊው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በርካታ ተጨባጭ ለውጦች የተመዘገቡበት ሲሆን፣ ለአብነትም የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን መቋቋም በሚያስችል መልኩ የተከናወነ እና ውጤቱም የተሳካ ሆኖ ቀጥሏል።
ብልፅግና ፓርቲ ይዞት ከተነሳው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ከማረጋገጥ አንፃር በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር የተሠራው ሥራ ተጠቃሽ ነው።
ከዚህ በፊት የዝናብ ወቅት ብቻ ይጠብቅ የነበረው የግብርና ሥራ መስኖና የበጋ እርሻን በመጠቀም፣ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በመከተል፣ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል ከፍተኛ ምርት ማምረት ተችሏል።
በተለይ በስንዴ እና ሩዝ ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች።
ከእርዳታ ተቀባይነት ወጥታም ወደ ላኪነት ተሸጋግራለች፡፡
በሌማት ትሩፋት የወተት፣ የዶሮ እና የማር ምርቶች የቤተሰብ ምግብ መሆን የቻሉ ሲሆን፣ በዚህም የዶሮ ሥጋ ምርት ከነበረበት 70 ሺህ ቶን ወደ 208 ሺህ ቶን፣ የወተት ምርት ከነበረበት ሰባት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሊትር ወደ 10 ቢሊዮን ሊትር፣ የማር ምርት ደግሞ ከ 129 ሺህ ቶን ምርት ወደ 272 ሺህ ቶን ለማሳደግ ተችሏል።
በቱሪዝም ገቢን የሚያሳድጉና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን ለዚህም ገበታ ለሸገር ፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ኮሪደር ልማቱን ማንሳት ብቻ ከበቂ በላይ ነው።
ተበላሽተውና ወደ ውድቀት እያመሩ የነበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችም በልዩ ክትትል በማጠናቀቅ ለፍሬ በቅተዋል፤ ለዚህም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋነኛ ማሳያ ነው።
በታምራት ቢሻው