AMN – ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም
በመገናኛ አካባቢ ያለውን ከፍተኛ የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመፍታት ያግዛል የተባለ የመሬት ውስጥ የእግረኛ መተላላፊያ መስመር ግንባታ ተጀምሯል፡፡
ከቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ መገናኛ ድረስ በሚዘልቀው የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ አካል የሆነው የእግረኛ መተላለፊያ ግንባታ ከዚህ ቀደም በቀለበት መልኩ የተገነባን የተሽከርካሪ ማሳለጫ ይበልጥ በማዘመን ለእግረኛ ምቹ የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑን የኮሪደር ልማት ስራውን የሚያስተባብሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገልጸዋል፡፡
የብዙዎች መተላላፊያ ከአንደኛው የከተማዋ ክፍል ወደሌላኛው መሻገሪያ የሆነውን መገናኛ ለአዲስ አበባ እንቅስቃሴ ያለውን ቁልፍ አበርክቶ ታሳቢ በማድረግ በአጭር ጊዜ ግንባታውን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ከንጋት እስከ ንጋት ይሰራልም ብለዋል አቶ ጥራቱ፡፡
ገንቢው ተቋራጭ የመገናኛ እግረኛ መተላላፊያ ዋሻ ግንባታን ለማጠናቀቅ 45 ቀናት እንደተሰጠውም ጠቁመዋል፡፡
የግንባታ ሂደቱን የሚያማክረው የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ይህንን በአይነቱ አዲስና ለየት ያለ የመንገደኛ መተላለፊያ መስመር ግንባታ ሂደት በተሰጠው ጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችል ግብዓት ስለመቅረቡም ገልጿል፡፡
መገናኛን ምቹና ለተሽከርካሪና እግረኛም የተስማማ በማድረግ 45 ቀናት የግንባታ ሂደት ውስጥም ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብርና ድጋፉን እንዲቀጥልም አቶ ጥራቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሰፊ የመንገድ ግንባታዎችን ያካተተው ከቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ መገናኛ ድረስ በሚዘልቀው የመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት ስራ ግንባታው የተጀመረው የመገናኛ የወስጥ ለውስጥ መተላላፊያ መስመርን ጨምሮ እግረኛን ከተሽከርካሪ ለይተው ማስተላለፍ የሚያስችሉ 3 የውስጥ ለውስጥ ዋሻዎች ግንባታን ያካተተ ነው፡፡
በአቡ ቻሌ