በመጪው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለመገንባት የተቀናጀ የኮሚኒኬሽን ሥራ ያስፈልጋል፡- አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ

AMN – ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም

ከወራት በኋላ በአዲስ አበባ በሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለመገንባት የተቀናጀ የኮሚኒኬሽን ሥራ እንደሚያስፈልግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን የገለፁት በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነባር ዲፕሎማቶችና በጎ ፍቃደኛ ካዴቶች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ተገኝተው በውጤታማ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ላይ ያተኮረ ስልጠና በሰጡበት ወቅት ነው።

በስልጠናው የተቀናጀ፣ የተደራጀ፣ ስትራቴጅክ እና አጀንዳ ሰጪ የኮሙኒኬሽን ስልትን በመከተል ውጤታማ የመንግስት ኮሙኒኬሽን እንዲኖር ሁሉም ዜጎች በብሄራዊ ስሜትና አገራዊ ሀላፊነት እንዲሰሩ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በመጪው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ኢትዮጵያን በሚገባ ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው ሰልጣኞቹ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተገቢው በመረዳት በሁሉም ዘርፍ እየታዩ ያሉ እምርታዎችን ለእንግዶቹ በማስገንዘብ አገራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ የሚያጠለሹና ብሄራዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ ሀሰተኛ መረጃዎችን በሚገባ በመለየት ብሔራዊ ጥቅምን ሊያስጠብቁ የሚችሉ የተግባቦት ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታውከዚህ በተጨማሪም አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ መልዕክቶችን በመቅረጽ ተሳታፊዎች ስለኢትዮጵያ በጎ መረጃ ይዘው እንዲመለሱ የሚያስችል የመረጃ ስራ በቅንጅት እንደሚዘጋጅ አሳውቀዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ሰልጣኞች በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት በሁሉም የኮሙኒኬሽን ስልቶች አገራቸውን ለማስተዋወቅ ያላቸውን ዝግጁነት ያሳወቁ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ላነሱት ጥያቄም ሚኒስትር ዴኤታው ምላሽ መስጠታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review