AMN ህዳር 23/2017 ዓ.ም
በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ለመኸር ሰብልና ድህረ ሰብል ስብሰባ አመቺ የሆነ ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው በሚቀጥሉት ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ እና የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች ከቀላል እሰከ ከመካከለኛ የዝናብ መጠን እንደሚያገኙ ጠቁሟል።
በአጠቃላይ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚኖረው ደረቅ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብና ለድህረ ሰብል ስብሰባ አመቺ መሆኑን ገልጿል።
ከሳምንቱ አጋማሽ በኋላ በተለይም በሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እሰከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ በትንበያው አመላክቷል።
በመሆኑም አርሶ አደሮች ይህንኑ በመረዳት ሳይዘናጉ በማሳ ላይ የሚገኙ የደረሱ ሰብሎችን ባሉት ደረቅ ቀናት እንዲሰበስቡ ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ባሉት ቀናት በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚጠበቀው ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት የበጋ ወቅት ሰብል ለሚያመርቱ ጥቂት የደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል።
በተጨማሪም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
በትንበያው መሰረት የሀገሪቱ የአየር ሁኔታ የገፀ ምድርና የግድቦችን የውሃ መጠን በማሻሻል ለበጋ መስኖ ውሃ አቅርቦት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ መጠቆሙን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።