AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም
“ሰንደቅ አላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን ፤ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የሰንደቅ አላማ ቀን በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ተከብሯል።
በዕለቱ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አማካሪና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የሠራዊት አባላት እና ስቪል ሠራተኞች ተገኝተዋል።
ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ በዚህ ወቅት፤ ሰንደቅ ዓላማችን ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ዘመን በማይሸረው የመሰዋዕትነት ውጤት የተገኘ የማንነታችን መለያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ስለ ሰንደቅና አላማው ክብርና ስለ ሀገሩ ከፍታ ሲል በዱር በገደሉ እየተዋደቀ መሰዋዕትነት ለሚከፍለው ወታደር ሰንደቅ ዓላማ ልዩ ትርጉም አለው ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወታደር፣ ሀገር እና ህዝብ ለመጠበቅ ቃል የሚገባው በሰንደቅ አላማው ፊት ነው ያሉት ጀኔራል መኮንኑ፤ የተሰጠውን ግዳጅ በአኩሪ ጀግንነት ፈፅሞ የሀገሩን አሸናፊነት የሚያውጀውም ሰንደቅ አላማውን ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ነው ሲሉ ገልፀዋል።