AMN- ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም
በምክክር ሂደቱ የጋራ ሀገርን የሚያጸኑ ሃሳቦችን በነጻነት አንስተናል ሲሉ በወላይታ ሶዶ ከተማ የሃገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ተናገሩ ።
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ያስጀመረዉ ምክክር እና የአጀንዳ መለየት ሂደት ሶስተኛ ቀኑን ይዟል ።
ከ96 ወረዳዎች 2ሺ ተወካዮች እየተሳተፉ በሚገኙበት ሂደት ተወካዮች ለሀገር ይበጃሉ ያሏቸዉ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተዉ ለይተዋል ።
ለቀጣይ የምክክር ሂደትም የሚወክሏቸዉን አካላት መርጠዋል ።
በክልሉ የሚገኙ 32 ብሄሮችን ወክለዉ እየተሳተፉ የሚገኙ ተወካዮችም ሂደቱ ሀሳቦቻቸዉን በነጻነት ማንሳት የቻሉበትና ዲሞክራሲን የተለማመዱበት መሆኑን ተናግረዋል ።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ምክክሩና የአጀንዳ ልየታዉ ከተጠበቀዉ በላይ ዉጤታማ እንደነበር አንስተዋል ።
ከተወካዮች የተሰበሰበዉን አጀንዳም ኮሚሽኑ በቀጣዩ እሁድ አጠናቆ የሚረከብ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል ።
በቀጣይ ከጥቅምት 22 ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፣የሲቪክ ማህበራትን እና የተቋማት ተወካዮችን ያሳተፉ ዉይይቶች እንደሚደረጉ ተመልክቷል ።
በአለማየሁ አዲሴ