በምዕራብ አርሲ ዞን የዶዶላና የሃሳሳ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን የሚፈቱ ስራዎች መከናወናቸውን የሃሳሳ ዶዶላ ከተሞች የመጠጥ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጀዋሮ ደቀቦ ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል እያካሄዱት ያለው የውሃ መሠረተ ልማት ስራዎች ጉብኝት እንደቀጠለ ነው።
በምዕራብ አርሲ ዞን የዶዶላና የሃሳሳ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ከውሃ አቅርቦቱ በተጓዳኝ እየተሰሩ ያሉ የተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ስራዎችም ተጎብኝተዋል።
የሃሳሳ ዶዶላ ከተሞች የመጠጥ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጀዋሮ ደቀቦ እንደገለጹት፣ ሁለት አዳዲስ የውሃ ፕሮጀክቶች ባለፈው አመት ተመርቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውንና ባሁኑ ወቅት በከተማም በገጠርም ህዝቡ ውሃ ለ24 ሰዓት እያገኘ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ውሃ በመሸጥ ብቻ ራሱን እንደማይችል ስለታመነ በጥናት ላይ በመመስረት የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን እየሰራን ነው ሲሉም አክለዋል።
የዶዶላ ከተማ የመጠጥ ውሃ እና ፍሳሽ ቅርንጫ ኃላፊ ሁሴን ዋሪዮ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ሃሳሳ ላይ የነዳጅ ማደያ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ይህም ተቋሙ በገቢ ራሱን እንዲያጠነክር እያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በቅርብ ጊዜም የንብ ማነብ ስራ መጀመራቸውን ጠቅሰው ከ70 በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በተቋሙ ሠራተኞች አቅም ገንብተው ስራ ማስጀመራቸውንና አበረታች ውጤት እየተገኘ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየታቸውን የሰጡ የዶዶላ እና የሃሳሳ ከተሞች ነዋሪዎች በነዋሪው ዘንድ የመጠጥ ውሃ ችግር ተነስቶ እንደማያውቅ በመጥቀስ አልፎ አልፎ በሚያጋጥም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ካልሆነ በስተቀር ለ24 ሰአት ውሃ እንደሚያገኙ መስክረዋል።
ተቋሙ ውሃ ከመሸጥ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ገቢዎች ራሱን ለመቻል የጀመራቸው የገቢ ማስገኛ ስራዎችን እንደሚደግፉም ተናግረዋል።
በምትኩ ተሾመ