AMN- ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም
በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከ23 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ምርቶች ኤክስፖርት መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
ነባር የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የማሸጋገር ስራ መከናወኑንም ኮሚሽኑ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ ክንውን ገምግሟል አካሂዷል።
በሩብ አመቱ 108 አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠቱን የገለጸው ኮሚሽኑ ከእነዚህ ውስጥም 65 ሙሉ በሙሉ የውጭ ባለሃብቶች፣ 24 የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በጥምርታ እና 24 የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ፍቃድ መውሰዳቸውን አመልክቷል።
በሌላ በኩል ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተከልሎ የነበረው የንግድ ዘርፍ ለውጭ ባለ ሃብቶች በመከፈቱ ምክንያት 78 ባለሃብቶች ፍላጎት ማሳየታቸው ተጠቁሟል።
ከባለሀብቶቹ 24ቱ የፍላጎት መግለጫ ሰነድ(ፕሮፖዛል) አቅርበው የ20ዎቹ በኮሚሽኑ ማኔጅመንት መፅደቁን ተገልጿል።
ፈቃድ ካገኙት ውስጥ 10 በገቢ ንግድ እና 10 በወጪ ንግድ የኢንቨስትመንት ፍቃድ በማውጣት ሂደት ላይ እንደሚገኙም ተመላክቷል።
በሩብ ዓመቱ ነባር የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የማሸጋገር ስራም መከናወኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት 131 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ኤክስፖርት መደረጉን አስታውቋል።
ከዚህም ውስጥ 23 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ከልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች፣ 108 ሚሊዮን ዶላር ከልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውጭ ኤክስፖርት የተደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በሩብ ዓመቱ የታየውን አፈጻጸም በቀጣይ ይበልጥ ለማጠናከር በጋራ መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።