AMN- ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ217 በጀት ሩብ ዓመቱ 367 ሺ ፓስፖርት ታትሞ ለደንበኞች መሰራጨቱን አስታወቋል።
አገልግሎቱ የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አስታውቋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የ2017 ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ በተቋሙ ላይ በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልፀው በሩብ ዓመቱ 367 ሺህ ፓስፖርት ታትሞ ለደንበኞች መሠራጨቱን አመልክተዋል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን በአዲስ መልክ በማቋቋም እና የኢሚግሬሽን አዋጅን ለማሻሻል በተሠሩ ሥራዎች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
በ2017 በጀት ሩብ ዓመትም ተቋሙ የሰው ኃይሉን ለማሳደግ 125 የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
የኦንላይን የፓስፖርት ምዝገባ በቀን ከሰባት ሺህ በላይ መድረሱን እና የመዳረሻ እና የአስቸኳይ ፓስፖርት አገልግሎቶ በቀን ከ600 በላይ የማስተናገድ አቅም መኖሩን ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
ተቋሙ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት እንደሚጀምር የተገለፀ ሲሆን ለዚህም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተመላክቷል።
በመሀመድ ኑር አሊ