በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ትልማችን ማሳኪያ አንዱ መንገዳችን የስንዴ ልማት ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN-ኅዳር 8/2017 ዓ.ም

በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ትልማችን ማሳኪያ አንዱ መንገዳችን የስንዴ ልማት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ዛሬ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረት እና ጅሩ ወረዳ በክላስተር የለማ የስንዴ ማሳን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በ1465.5 ሄክታር ላይ የለማው የስንዴ ሰብል በሶስት ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን በክላስተር ያስተሳሰር መሆኑን የገለፁ ሲሆን በትብብር መስራት አዋጭ መሆኑን ያሳየ ድንቅ ክዋኔ ነውም ብለዋል፡፡

በክልሉ በዘንድሮ ዓመት ከምንጊዜውም በላይ ማዳበርያን ጨምሮ ከፍተኛ የግብርና ግብዓቶች አሰራጭተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ለአርሶ አደሮች ምርታማነት ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡

“እንደ ሀገር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ እና ስርዓተ ምግብ አቅማችንን ለማሳደግ ከፍተኛ የምርት ዕድገት ማስመዝገብ ችለናል” ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

“በስንዴ ራስን ለመቻል የተቀመጠውን ሀገራዊ ግብ ማሳካታችን የበለጠ አበረታች በመሆኑ ዘንድሮም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በምርት ዘመኑ የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል አድርገናል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review