በርካታ የተሽከርካሪ ዕቃዎች ከ5 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም

በልደታ ክ/ከተማ በተደረገ ጥናት በርካታ የተሽከርካሪ ዕቃዎች ከ5 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ሱማሌ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

የጎማ ቁጠባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በክ/ከተማው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መነሻ በማድረግ ተከታታይነት ያለው የወንጀለኞች ጥናትም እያደረገ ይገኛል።

በዚህም መሠረት ህጋዊ የመበርበሪያ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት በማውጣት በጥናት ላይ በተመሰረተ ክትትል በሁለት መኖሪያ ቤቶች ውስጥና በአንድ ሱቅ ውስጥ በተደረገ ፍተሻ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሠረቁ የተሽከርካሪ ዕቃዎችን ከሌቦች እየገዙ በማስቀመጥ መልሰው ለህብረተሰቡ ለመሸጥ የተከማቹ በርካታ የተሽከርካሪ ዕቃዎች ከ5 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በዚህም መሰረት 48 የተለያዩ የተሽከርካሪ ስፖኪዮዎች፣ 8 የተሽከርካሪ ሴንተራል ሎክ፣ 6 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጀር ክዳንና ልዩ ልዩ የተሽከርካሪ ዕቃዎች የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ካከማቹ ግለሰቦች ተይዘው ምርመራውም መቀጠሉን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል ።

በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ተፈፅሞብኛል የሚል ግለሰብ ልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በአካል በመቅረብ መረጃ መስጠት እንደሚችልም መጠቆሙን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተለያዩ ጊዚያት በተለያዩ ክ/ከተሞች የተሠረቀ ንብረት በሚገዙና በሚያከማቹ ግለሰቦች ላይ በህግ አግባብ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በርካቶች ተጠያቂ መደረጋቸውን ገልፆ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review