በርካታ ገንዘብ የያዙ በማስመሰል የማጭበርበር ወንጀል ሊፈጽሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
AMN – ሚያዝያ 09/2017
በርካታ ገንዘብ የያዙ በማስመሰል ከፊትና ከኋላ ሁለት ሁለት መቶ ብሮች በማድረግና ባለ አስር ብሮችን በመጠቅለል የማጭበርበር ወንጀል ሊፈጽሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በግል ተበዳይ ጠቋሚነት በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።
ግለሰቦቹ ሆን ብለው በመዘጋጀት በርከት ያለ ገንዘብ የያዙ ለማስመሰል በሁለት መቶ ብሮች የተጠቀለሉ ባለ አስር ብር ኖቶችን በመያዝ የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሰዎች ላይ የሚያዩትን ጌጣ ጌጥ አታለው በገንዘቡ ለመቀየር ካልሆነም የበለጠ ገንዘብ የሚያገኙበትን ዘዴ ይፈጥራሉ፤ ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ የሚፈፀሙት የወንጀል ድርጊት መሆኑን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል፡፡

የግል ተበዳይ በፍጥነት ነቅታባቸው ባይያዙ ወደ ባንክ ወይም ወደ ኤ.ቲ.ኤም ይዘዋት በመሄድ ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት ገንዘብ ሊያስወጧት እንደነበርም ፖሊስ ገልጿል።
የግል ተበዳይ ለፖሊስ በሠጠችው ጥቆማ መነሻነት ምርመራው የቀጠለ ሲሆን ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ የወንጀል አፈፃፀም የጣት ቀለበት የተወሰደባት ሌላ ግለሰብ መረጃ ለመስጠት ወደ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደመጣች ታውቋል፡፡ ሌሎች ተመሣሣይ ወንጀል ተፈፀሞብናል የሚሉ ለየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ መረጃ መስጠት እንደሚችሉ ፖሊስ አስታውቋል።