በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የገዘፈ ስምና ዝና ያላት ኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ነባራዊ ሁኔታዋ የሚደነቅና የአፍሪካ ኩራት የሚሆን ነው: -የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች

You are currently viewing በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የገዘፈ ስምና ዝና ያላት ኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ነባራዊ ሁኔታዋ የሚደነቅና የአፍሪካ ኩራት የሚሆን ነው: -የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች

AMN- ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የገዘፈ ስምና ዝና ያላት ኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ነባራዊ ሁኔታዋ የሚደነቅና የአፍሪካም ኩራት የሚሆን ነው ሲሉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የመጀመሪያው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም!” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የመከላከያ ሚኒስትሮቹ ከጉባዔው ተሳትፎ በተጨማሪ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ጎብኝተዋል።

በትናንትናው እለት በቢሾፍቱ የሚገኘውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የጎበኙ ሲሆን፤ በዛሬው እለት ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን ጎብኝተዋል።

የዩጋንዳ እና ሴኔጋል የመከላከያ ሚኒስትሮችና የደቡብ አፍሪካ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር የኢትዮጵያን አየር ኃይልና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን አድንቀዋል።

በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የገዘፈ ስምና ዝና ያላት ኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ነባራዊ ሁኔታዋ የሚደነቅና የአፍሪካም ኩራት የሚሆን ነው ብለዋል።

የዩጋንዳ የመከላከያ ሚኒስትር ጃኮብ ኦቦዝ፤ በአፍሪካ የሰላም፣ ነፃነትና የጋራ ልማት ሥራዎች የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና ተጠናክሮ መቀጠሉን በተግባር አረጋግጠናል ነው ያሉት።

በተለይም በአህጉራዊ የሰላም ማስከበር ሂደት የኢትዮጵያ ሚና እና ተሳትፎ የላቀ መሆኑን አስታውሰው፤ በጥረቷ መቀጠል እንዳለባትም ገልጸዋል።

የሴኔጋል የመከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ቢራሜ ዲዮፕ፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የላቀ ሚናዋን እየተወጣች ያለች አገር መሆኗን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተመለከትነው የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ነባራዊ ሁኔታም የሚደነቅና የሁላችንም ኩራት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በአህጉራዊ የኢኮኖሚ እድገትና የጋራ ልማትም የኢትዮጵያ ጥረት የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑንም አንስተዋል።

የደቡብ አፍሪካ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሜጀር ጄኔራል ባንቱ ሆሎኒሳ፤ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያን ሚና ማንም ሊዘነጋው የሚችል አይደለም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታችን በመከላከያና የደኅንነት ተቋማት ጉብኝታችን የተመለከትነው በቀጣይ የኢትዮጵያን ሚና የሚያጠናክር ስለመሆኑም ተገንዝበናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review