በሰመራ ከተማ በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የተገነቡ ሁለት ዘመናዊ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ተመርቀዋል፡፡
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ከለውጡ በኋላ ለኢንዱስትሪና ለኢንቨስትመንት ዘርፉ በተሰጠ ትኩረት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው ።
ዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለሃገር እድገትና ብልፅግና ጉዞ ማሳለጫ መንገድ መሆኑን ገልፀዋል።
በአካባቢ የሚገኝን የተፈጥሮ ፀጋን በመጠቀም ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል” ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ
ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ክልሉ ጨውን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት መገኛ መሆኑን ጠቁመው ዛሬ ተመርቀው ስራ የጀመሩ ፋብሪካዎችን የበለጠ ለማጠናከር አስፈላጊው ትብብርና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን በበኩላቸው እንደገለጹት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል ።
በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያልተነኩ ሐብቶች ያለው በመሆኑ ባለሀብቶች በዘርፍ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል ።
ዛሬ ከተመረቁት ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው የአፍሮ ትሬዲንግ ዋና ስራ አሰኪያጅ አቶ ሙክታር መሐመድ እንደገለፁት ፋብሪካው በወር 250 ሺህ ኩንታል በአዮዲን የበለፀገ ጨው የማምረት አቅም አለው።
ፋብሪካው በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ መገንባቱን ጠቁመው በቀጣይነት ተጨማሪ የገበታ ጨው ማምረት እንደሚጀምር አመላክተዋል።
ፋብሪካው ለ200 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቀዋል፤
ሌላው በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ስራ የጀመረው የአል አልሳ ጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሐመድ ፋብራካው ለ208 ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን መግለፃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የኢትዮጵያ ምግብና መድሐኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ፣ የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል