በስም ልክ መፍካት

አዲስ አበባ ስንፍናን እምቢኝ፤ እንቅልፍ ይቅርብኝ ያለች ከተማ እየሆነች መጥታለች በሚለው ሀሳብ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የጤና ችግር፣ የስራ አጥ፣ የጽዳት፣ የትራንስፖርትና መሰል ችግር ተሸክሞ እረፍት እንዴት ይታሰባል ነው ነገሩ፡፡ ለዚህም ለዓመታት ከተኛችበት እንቅልፍ ነቅታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ስሟን የሚመጥን ስራዎችን ስተሰራ ቆይታለች። በኮሪደር ልማት ስራውም በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ መዲናዋ ሌላ መልክ ይዛለች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በእርግጥ ሶስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በዚህ ልክ መፍካት እንደሚጠበቅባት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ መዲናዋ አንገቷን ቀና እንድታደርግ በጉያዋ ሸሽጋ ይዛቸው የነበሩ ችግሮቿንም የኮርደር ልማት በተሰኘ ድንቅ ሀሳብ እልባት እንዲያገኙ በመትጋት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህም የከተማ ውበት፣ የህንጻ ደረጃዎች እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች መልክ እንዲኖራቸው አድርጋለች፡፡

ከተማዋ ለነዋሪዎች የተመቸች፣ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎችን በብቃት ትወጣ ዘንድ የተለያዩ የልማት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህም ውሰጥ የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ አንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ ወዳጅነት አደባባይን ጨምሮ የተለያዩ ፓርኮችና አደባባዮች፣ ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃያሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል፣  መስቀል አደባባይና፣ የቤተ መንግስት ፓርኪንግን የመሳሰሉ የህዝባዊ በዓላት ማክበሪያና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የምገባ ማዕከላት፣ የአረጋውያን ማቆያ ማዕከል፣ የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራ፣ የዳቦና እንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካዎች እንዲሁም በቅርቡ እየተፋጠነ የሚገኘው ዘርፈ ብዙው የኮሪደር ልማት ስራ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

በተጨማሪም በሰው ተኮር እና በጎ ፍቃድ ስራዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራት፣ በጤናው ዘርፍ የእናቶችንና የህጻናትን ጤና ለማሻሻል፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የትምህርት ተሣትፎ፣ ፍትሐዊነትና ጥራትን ለማሳደግ፣ መሬት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ማዘጋጀትና የልማት ስራዎችን ማፋጠን ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም ሰሞኑን በተካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ላይ በሰጡት ማብራሪያ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ተልኮዎችን በብቃት መወጣት የምትችል ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ አመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት የከተማ አስተዳደሩ በበጀት አመቱ ያከናወናቸው የኮሪደር ልማት እና ሌሎች ዋና ዋና የፕሮጀክት አፈጻጸም ስራዎችን ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የዝግጅት ክፍላችንም ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ ያቀረቡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሚናዋን በብቃት የምትወጣ ለማድረግ እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎች ምን መልክ አላቸው? የመዲናዋ የወደፊት የቤት ስራስ ምን ሊሆን ይገባል? ሲል የተለያዩ ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን መምህር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) በሰጡን ማብራሪያ፣ አዲስ አበባ ከተማ እስከ አሁን ባሉት ጊዜያት አስር መሪ ፕላኖች እንደነበሯት ገልጸው፣ አስሩም የነዋሪውን ችግር በአግባቡ ፈትተዋል ማለት ባይቻልም የከተማ አስተዳደሩ አሁን እየተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን የተሻለ ገፅታ እያላበሳት ይገኛል ብለዋል፡፡

ዳንኤል (ዶ/ር)፣ አዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት የመንገድ ልማት ስርዓትን ያልተከተለች እንደነበረች ጠቁመው፣ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች በቅጡ ያልተሟሉላት ነበረች፡፡ የኮሪደር ልማቱ እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ነዋሪው በምቾት እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

አዲስ አበባ እንደ ከተማ ሶስት አካላትን የምትወክል ከተማ መሆኗን የጠቆሙት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የምታስተናግድ ከተማ ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት ዋና መቀመጫ መሆኗን አውስተዋል፡፡ ከጄኔቭና ከኒው ዮርክ ቀጥላም ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ዳንኤል (ዶ/ር) አዲስ አበባ ትልቅ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ከተማ ስለሆነች በዚህ ልክ የመዋቅር፣ የከተማ ፕላን እና አሰራር የምትፈልግ መሆኗን ጠቅሰው፣ በቅርብ ጊዜ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና መሰል የልማት ስራዎች ለዚህ ግብዓት እንደሚሆኑ አንስተዋል፡፡

አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊያን የሚዝናኑባት ከተማ እንድትሆን፣ አፍሪካዊያንም በዚያ ልክ እንዲያዩዋት፣ የመላው ዓለም ዲፕሎማቶች መቀመጫ መሆኗን በሚገልጽ መንገድ እየተሰራች መሆኑን ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ የከተማዋ የኮሪደር ልማት ስራና  ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች የስራ ባህልን ቀይረዋል፡፡ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ማድረግ ይቻላል እንዴ?’ ያስባሉ ሀሳቦች መንጭተው ወደ ተግባር ተቀይረዋል። ይህም ከተማዋ ለመላው የኢትዮጵያ ከተሞች ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ እሴቶች እንዲኖሯት አድርጓል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሽመልስ ኃይሉ፣ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ከተማ መሆኗን አውስተው፣ ሆኖም በዚያ ልክ ለዲፕሎማቶች፣ ለቱሪስቶች፣ ለኢትዮጵያውያንም ምቹ የሆነች ከተማ እንዳልነበረች ይገልጻሉ፡፡ በተለይም ከተማዋ ፕላን ይጎድላት እንደነበርና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷ ውዝግብ የተሞላበት እንዲሆን ያደረገውም ይህ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በዚሁ ምክንያት የቀድሞው የሊቢያ መሪ የነበሩት ሙሃመር ጋዳፊ አዲስ አበባን ከትሪፖሊ የቆሻሻ መጣያ ጋር እያመሳሰሉ ሲገልጿት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ከተማዋን ለዲፕሎማቶች ብቻ ሳይሆን ለከተማዋ ነዋሪዎች እና ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ምቹና ሁሉን አቀፍ ከተማ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አመርቂና ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የመከሩት መምህር ሽመልስ፣ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉም በማብራሪያቸው ገልጸዋል፡፡

በእርግጥ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በምክር ቤት ቆይታቸው የመዲናዋ ቀጣይ አቅጣጫዎች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡ ከንቲባዋ በቀጣይ የሁሉንም ርብርብ የሚሹ ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ሲያብራሩ፤ “የተጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም አጠናክሮ የማስቀጠል፣ በሁሉም መስክ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በማሻሻል የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ አካባቢን መፍጠር፣ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ሀገራዊ፤ አህጉራዊና አለም አቀፍ ሚናዋን በብቃት የምትወጣ፤ ስሟና ግብሯ የተናበበ ስማርት ከተማ እንድትሆን የተጀመረው ልማት በጥራት፣ በስፋትና በፍጥነት ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡

ከተማዋ ወጥ የሆነ አሰራር በመከተል ለዜጎቿ ምቹ የመዝናኛ እና የኮንፈረስ ማዕከል እንድትሆን መስራት፣ በመንገድ፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴል እንዲሁም በቂ የመኖሪያ ቤቶች፣ ከተማዋን የዜጎቿ፣ የአፍሪካውያን እና ለመላው የዓለም ሀገራት ዲፕሎማቶች ምቹ የመኖሪያ፣ መዝናኛ እንዲሁም የኮንፈረስ ማዕከል እንድትሆን በቀጣይነት መስራት ያስፈልጋል የሚለው ሀሳብ ደግሞ የመምህር ሽመልስ ነው፡፡ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በግል ዘርፉ፣ በሕብረት ሥራ ማኅበራት፣ በመንግስትና በግል የአጋርነት ፕሮግራም በስፋት ተግባራዊ እንደሚደረግ ከንቲባዋ መግለጻቸውን ደግሞ እዚህ ጋር መጥቀስ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

በከተማዋ አሁን እየታየ ያለው የልማት ጅማሮ አስደሳች ነው የሚሉት መምህር ሽመልስ፣ ሁሉንም አካባቢዎች ማዕከል ባደረገ መልኩ ልማቱ ሊከናወን እንደሚገባና የከተማ መዋቅራዊ ፕላን፣ የመንገድ፣ የትራስፖርት፣ የመኖሪያ ቤት ለዜጎቿ የበለጠ ምቹ ማድረግም የኮሪደር ልማት ስራው በሁሉም የመዲናዋ አካባቢዎች እንዲዳረስ መሰራት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ከተማዋ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎቿ ቁጥር ስለሚጨምር ይዞት የሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ትሩፋትም ቀላል አይሆንም፡፡ በተለይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ ሰፊ ዕድል ስለሚፈጥር የኮንፈረስ ቱሪዝም ለከተማዋ ገቢ ያመጣል፤ ሀገሪቷን ያስተዋውቃል፤ በሌላ መንገድ ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከቱሪዝም ገቢ የሚያገኙበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በቴክኖሎጂ፣ በአሠራርና በአደረጃጀት በማስደገፍ እና ተግባራዊ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥና የከተማዋን መልካም አስተዳደር በላቀ ደረጃ በማሻሻል በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ያተገኘውን ድል በአገልግሎት አሰጣጥ እና በመልካም አስተዳደርም ለመድገም እንተጋለን ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡

በመሆኑም አሁን የሚታዩ እና የተጀመሩ ልማቶች በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ አምስት እና ከዚያ በታች በሆነ ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባን በዓለም ላይ ከምናያቸው ጥሩ ገጽታ ካላቸው ከተሞች አንዷ እንደምትሆን የሚያሳይ ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተማዋ ለነዋሪዎቿ የተመቸች እንድትሆን ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሰው ተኮር እና በጎ ፍቃድ ስራዎች 1 ነጥብ 7 ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። 21 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ 35 ሺህ 600 ዜጎች እየተመገቡ ይገኛሉ። 1 ሺህ 504 ነጥብ 27 ሄክታር መሬት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በማዘጋጀት የልማት ስራውን ማገዝ ተችሏል፡፡ 18 ሺህ 91 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review