AMN ኅዳር -30/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ በስራ እድል ፈጠራ እና በሌማት ቱሩፋት ስራዎች ከ35 ሺ በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉ የሚበረታታ መሆኑንበምክትል ከንቲባ ማእረግ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሞገስ ባልቻ አስታወቁ ፡፡
የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ባለፉት አምስት ወራት በተለይም የህዳር ወር በስራ እድል ፈጠራ እና በሌማት ቱሩፋት የተሰሩ ስራዎች ግምገማ አካሂዷል።
በግምገማው ባለፉት አምስት ወራት ከወረዳ ጀምሮ በስራ እድል ፈጠራ ፣ በከተማ ግብርና ፣ በኢንተርፕራይዞች ማደራጀት እና በሌማት ትሩፋት የተሰሩ ስራዎች እና የወደፊት እቅድን የሚያሳዩ ሶስት ሪፖርቶች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማእረግ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሞገስ ባልቻ በአዲስ አበባ ከተማ በስራ እድል ፈጠራ እና በሌማት ቱሩፋት ስራዎች ከ35 ሺ በላይ ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አበረታተዋል።
በስራ እድል ፈጠራው የታየው ስኬት የአመራሩ ትኩረት ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ኋላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያሳዩ ክፍለከተሞች እና ወረዳዎች ክፍተቶቻቸውን ሊፈትሹ ይገባልም ብለዋል።
በግምገማው ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የክፍለ ከተማ ፣ የወረዳ አመራሮች እና ሴክተር መስሪያ ቤቶች መሳተፋቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
በአሸናፊ በላይ