በቅርቡ ሴዳበርግ ትራቭል የተሰኘው ገጸ-ድር ባስነበበው ጽሁፍ በመፀው (ጥቅምት፣ ህዳር እና ታህሳስ) መጎብኘት አለባቸው በሚል አምስት የአፍሪካ ሃገራትን ዘርዝሯል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም መረጃውን መነሻ በማድረግ ጉዳዩን እንደሚከተለው ዳስሶታል፡፡
የክረምቱን ወር አልፎ የመፀው ወራት መምጣት በሰዎች ስሜት ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም ላይ ለውጦችን ይዞ ይመጣል። አበቦች አብበውና ፈክተው፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ፣ ሰማይ በሐምራዊ ቀለም ደምቃ የምትታይበት ወቅት ነው፡፡ መፀው ስሙ እንደሚያሳየው አበባ ማለት ነው። መገኛው ግስ መፀወ ሆኖ አበበ፤ አበባ ያዘ ማለት ነው። አበባና ነፋሻማ አየር ቀላቅሎ የያዘው ይህ ወቅት ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25 ይሸፍናል። ሴዳበርግ ትራቭል ገጸ-ድርም ይህንን መነሻ በማድረግ ነው በመጸው መጎብኘት አለባቸው ሲል የሚከተሉትን ሃገራት የዘረዘረው፡፡
ኢትዮጵያ
በመጸው ወቅት በውብ ተፈጥሮ እየተደመሙ ታሪካዊ ቅርሶችን መጎብኘት ለሚወዱ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ ተመራጭ ሃገር ነች ይላል፤ የሴዳበርግ ትራቭል መረጃ። በተለያዩ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ንብረት የምትታወቀው አገር ኢትዮጵያ በታሪካዊ ቅርሶችዋ ይበልጥ ትታወቃለች ይላል፤ ይኸው መረጃው፡፡ በታሪካዊ ቤተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች፣ ሃውልቶች፣ ብርቅዬ የዱር አራዊትና አዕዋፍት ኢትዮጵያን ተለይታ የምትታወቅባቸው መገለጫዎቿ ናቸው ሲል መረጃው አክሏል፡፡

በመረጃው መሰረት፣ ከኢትዮጵያውያን ቀደምት የስልጣኔ አሻራዎች መካከል አንዱ የአክሱም ሃውልት ነው፡፡ የሃውልቱ ጎን የመስኮት ቅርጽ የያዙ ፍልፍሎች ሲኖሩት፣ በመጨረሻው ጫፍ ላይ ደግሞ በብረት ፍሬም የታገዘ የግማሽ ክብ ቅርጽ ይዟል፡፡ የአክሱም ሃውልትን መጎብኘት የሰው ልጅ የስልጣኔ ታሪክ ከየት ተነስቶ እዚህ እንደደረሰ ለማወቅ ጥሩ አብነት ነው፡፡
በመፀው መጎብኘት ያለበት ሌላኛው ቅርስ ደግሞ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ነው ይላል፤ ይኸው ገጸ-ድር፡፡ ከአንድ ወጥ አለት በርና መስኮት እንዲኖራቸው ተደርገው የተሰሩት የላሊበላ ወቅር አብያተ-ክርስቲያናት ትልቅ የስልጣኔ አሻራዎች ናቸው። ከዚህ አንጻር ቱሪስቶች ሊጎበኙት የሚገባ ታሪካዊ ቅርስ ነው። ሌላኛው በመፀው መጎብኘት ያለበት ቅርስ ደግሞ የጀጎል(የሐረር) ግንብ ነው፡፡ በታሪካዊቷና የመቻቻል ተምሳሌት በሆነችው ሐረር ከተማ ውስጥ የሚገኘው የጀጎል ግንብ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበችው ሌላኛው ታሪካዊ ቅርሰ ነው። እነዚህንና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶችና የተፈጥሮ መስህቦች በተለይ በመፀው ወቅት ሊጎበኙ ይገባል ሲል የሴዳበርግ ትራቭል መረጃ ያስገነዝባል፡፡የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባም የወጭ ጎብኚዎችን ብቻ ሳይሆን የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ጭምር የሚስቡ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ነች፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰሩት እንደ የአድዋ መታሰቢያ፣ አብርሆት ቤተ-መጻህፍት፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ ውብ ፋውንቴኖችና በእግር መንሸራሸር ለሚወድዱ ጎብኚዎች ምቾት የሚሰጡ ጎዳናዎች የአዲስ አበባን ልዩ መገለጫዎቿ ናቸው፡፡ ከታሪካዊ ቅርሶችና ሙዚየሞች በተጨማሪ መንፈስን በሚያድሱ የቱሪስት መስህቦች እየጎበኙ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ለሚፈልጉ ቱሪስቶች አዲስ አበባ ምቹ ከተማ ነች። ከዚህ አንጻር ጎብኚዎች አዲስ አበባን ቢጎበኙ ልዩ ትውስታን ይዘው ወደ ሃገራቸው መመለስ ይችላሉ፡፡
ደቡብ አፍሪካ
በሃገረ-ደቡብ አፍሪካ በተለይ በሰሜን ማፑቱላንድ በመፀው ወቅት ለጎብኚዎች እጅግ ምቹ ነው ይላል፤ የሴዳበርግ ትራቭል መረጃ። ህብረ-ቀለም ያላቸው ዕጽዋቶችና አዕዋፋት በስፋት የሚታዩበት ወቅት ነው፡፡ እንዲሁም ልዩ ልዩ የኤሊ ዝርያዎች በመፀው ወቅት በስፋት የሚታዩበት ነው፡፡
በመፀው ወራት ደቡብ አፍሪካዊቷ ሃገር የባህር ዳርቻዎቿ በውብ ነፋሻማ አየርና ሞቅ ባለ ጸሃይ ታጅበው የጎብኚዎችን ስሜት ሰቅዘው ይይዛሉ፡፡ ከእነዚህ ውብ የባህር ዳርቻዎች በተጨማሪ፣ ውብ የሆኑ ከተሞቿና ሌሎች ተፈጥሯዊ መስህቦቿ ለቱሪስቶች ምቹና ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በአብዛኛው የምትታወቀው በፀሃያማ የአየር ንብረቷ ሲሆን፤ ጎብኚዎች ዝናባማ ወራቶች እስኪያልፉ ድረስ ወደዚህች ሃገር መጥተው የሚዝናኑባት የቱሪስት መዳረሻ ነች።
ናሚቢያ
ናሚቢያ ተፈጥሮ ካደመቀቻቸው የአፍሪካ ሃገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ጥንታዊ በሆነው በናሚቢያ በረሃ ውስጥ ያለው አስደናቂ ትዕይንትና ተፈጥሮ የጎብኚዎችን ቀልብ ሰቅዞ ይይዛል። ጎብኚዎችም በዚህ በናሚቢያ በረሃን ከመጎብኘት ጎን ለጎን የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችን ለመመልከት ስፍራውን ይመርጡታል ይላል፤ የሴዳበርግ ትራቭል መረጃ፡፡
ናሚቢያ በርካታ መንፈስን ማሳረፊያ ስፍራዎች አሏት፡፡ በተለይ በፅሞና ተፈጥሮን ማድነቅ ለሚወዱ ጎብኚዎች የሚመርጧት አፍሪካዊት ሃገር ነች፡፡ በመጸው ወራት ናሚቢያ የተፈጥሮን ውበት ጎልቶ የሚታይባት ሃገርም ነች፡፡ ለጎብኚዎች ምቹ የሆነችው ናሚቢያ፣ በተለይ ብርቅዬ የዱር አራዊቶችን በቅርበት ሆነው መመልከት ለሚወዱ በጣም ተመራጭ ሃገር ነች፡፡ ምክንያቱም የዱር እንስሳትን ለመመልከት የሚያስችል የተመረጡ ስፍራዎችና ሰገነቶች ስላሉ ጎብኚዎች ዘና ብለው ብርቅዬ እንስሳቶችን ለመመልከት እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ናሚቢያ በተፈጥሮ መስህቦች የታደለች ሃገር በመሆኗ በመፀው ወቅት በቱሪስቶች ልትጎበኝ ይገባል በሚል ከተመረጡት የአፍሪካ ሃገራት መካከል አንዷ መሆን ችላለች፡፡
ሞሪሸየስ
በህንድ ውቅያኖስ ውስጥ በተርክዬ ይስ ውሃ ዳርቻ እንደ ውብ ጌጣጌጥ አጊጠው በተቀመጡት ቅንጡና ማራኪ ደሴቶቿ ይበልጥ ትታወቃለች፤ ሞሪሸየስ፡፡ እንዲሁም ሰፋፊ የእግር ጉዞ የሚደረግባቸው ዳርቻ ያላቸው ሃይቆችና በአይነታቸው ለየት ያሉ ደማቅ አበቦች ሌላኛዎቹ የሞሪሸስ ድምቀቶች ናቸው። ፏፏቴዎችን እና ብርቅዬ አዕዋፍትን የሚያሳዩ ሰገነቶች እንዲሁም በአረንጓዴ ቀለም ባጌጡ ደኖች የተከበቡ ተራሮች የጎብኚዎችን ቀልብ በቀላሉ የሚይዙ መስህቦች ናቸው። ከዚህ አንጻር በመጸው በባህር ዳርቻዎች ውስጥ በሚገኙ ቅንጡ የመዝናኛ ስፍራዎች እየተንሸራሸሩ ጌዜያቸውን ማሳለፍ ለሚፈልጉ ጎብኚዎች ሞሪሺየስ ተመራጭ ሃገር ነች ሲል መረጃው አስነብቧል፡፡
ኬንያ
የሴዳበርግ ትራቭል ገጸ-ድር በመጸው ወቅት መጎብኘት አለባት በሚል የመረጣት ሌላኛዋ ሃገር ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ኬንያ ነች፡፡ በተለይ ህዳርና ታህሳስ ወር የኬንያ የባህር ዳርቻዎች ነፋሻማ አየራቸው በቱሪስቶች ይበልጥ ይወደዳል። በእግር መንሸራሸር ለሚሹ ጎብኚዎችም ይህ ወቅት ጥሩ ተመራጭ ነው ይላል መረጃው፡፡
ሌላው በኬንያ የሚገኘው የማሳይ ማራ ብሔራዊ ፓርክ በዚህ ወቅት መጎብኘት ያለበት ስፍራ እንደሆነችም የሴዳበርግ ትራቭል መረጃ ያስገነዝባል፡፡ ይህ ዝነኛ የመዝናኛ ስፍራ አንበሳዎች፣ ዝሆኖች፣ ቀጭኔዎች እና የሜዳ አህያዎችን ጨምሮ የተትረፈረፈ የዱር አራዊት መገኛ ሲሆን ይህም የዱር እንስሳት አድናቂዎች በስፋት የሚጎበኙት ቦታ ያደርገዋል። ጎብኚዎች የማሳይ ማራ ቤት ብለው የሚጠሩትን አስደናቂ የዱር እንስሳት ስብጥር ለማየት ወደዚህ ስፍራ ሲመጡ፣ ምቹ አየር እየወሰዱና በእግር በመንሸራሸር ለመዝናናት በጎብኚዎች የሚዘወተር አካባቢ ነው።
በአብርሃም ገብሬ