AMN – ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም
በስንዴ ምርትማነት ላይ የተከተልነው ስትራቴጂያዊ አካሄድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ብዝሃ ምርትና እና ምርታማነት ለመጨመር እክል ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ እጥረት ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ በሚገኘው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ኮንፍረንስ ላይ ገልጸዋል።
የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የእርሻ መስፋፋት ለአፈር መሸርሸር፣ ለመሬት መራቆት እና ለደኖች መመናመንን ማስከተሉን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ትራንስፎርሜሽን እና በምርታማነት ላይ ትኩረት ሰጥተን በሠራነው ሥራ የሚታረስ መሬት በእጥፍ እንዲጨምር አስችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የኢንዱስትሪ ሰብሎች መመረታቸው ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ማሽላን የመሳሰሉ ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችንም በስፋት በማምረት አመርቂ ውጤት አግኝተናል ሲሉ ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ምርታማነትን ለመጨመር ዓላማ ተደርጎ በ2019 በተጀመረው እና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም አካል በሆነው በአረንጓዴ አሻራ ሥራ እስከአሁን 40 ቢሊዮን ችግኞችን መተከላቸውን ተናግረዋል።
ይህም በ2026 ወደ 50 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘው ዕቅድ አካል መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዚሁ ፕሮግራም በመመራት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የደን ሽፋናችንን ከ6 በመቶ በላይ አሳድገናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህም ሥነ-ምኅዳር እንዲያገግም፣ የአፈር ለምነት እንዲጨምር እና ዘላቂ የግብርና ሥራ እንዲኖር ማስቻሉን አብራርተዋል።
በስንዴ ምርትማነት ላይ የተከተልነው ስትራቴጂያዊ አካሄድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መስኖን በማስፋፋት እና የግብርና ሥራን በማዘመን ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ አምርታለች ብለዋል።
ከአጠቃላይ የስንዴ ምርት መካከል 130 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ በማልማት የመጣ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ የግብርና የኢንዱስትሪ ፖርኮችም ምርት መከማቻን በማመቻቸት፣ ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ገበያን በማፈላለግ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ተጫውተዋል። በዚህም ምክንያት ከምርት ሂደት በኋላ የሚወጣን ኪሳራ በ30 በመቶ መታደግ ተችሏልም ነው ያሉት።
ይህ በመሆኑም የአርሶ አደሩን የገቢ መጠን በ20 በመቶ ማሳደጉን እና በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
አክለውም ምንም እንኳ የዋጋ ግሽበት፣ የኢኮኖሚ መዋዠቅ እና የሚለዋጥ የዓለም ሁኔታ ቢኖርም ሀገራዊ ድህነትን ለመቀነስ ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ እንደገኛለንም ነው ያሉት።
ዓለምን ከረሃብ ነፃ ለማውጣት ኋላ ቀር ከሆነው የግብርና አስተራረስ ልምምዳችን በመውጣት የምግብ ሥርዓታችንን በማስተካከል የግብርና ኢንዱስትሪን መጠናከር ኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል።
ይህም በግብርና ግብዓቶች፣ በኃይል አቅርቦት እና በቴክኖሎጂ ላይ አተኩሮ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ለስኬቱም መንግሥት፣ የግል ሴክተሮች፣ አርሶ አደሮች፣ ተማራማሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ በማጠቃለያ መልእክታቸው ላይ አስታውቀዋል።
በማሬ ቃጦ