በስፖርት ማዘውተሪያዎች ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች

You are currently viewing በስፖርት ማዘውተሪያዎች ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች

አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ርቀት ከተጓዘችባቸው መስኮች መካከል አንዱ መዲናዋ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የላትም የሚውን ጥያቄ ለመመለስ ያደረገችው ጥረት ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ጉዳዩን በማስረጃ ስናስደግፈው ደግሞ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከአራት ዓመታት ወዲህ በስፖርቱ ቤተሰብ ለሚነሱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ርቀት ስለመሄዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያሳያል። በአዲስ አበባ ከተማም ከ1 ሺህ 300 በላይ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዳሉ የቢሮው መረጃ ያትታል፡፡ በመንግሰት፣ በግልና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየተዳደሩ ያሉ አጠቃላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራች ቆጠራ መደረጉን የሚገልጸው ቢሮው፣ በቅርቡ ትክክለኛ ቁጥራቸውን ይፋ እንደሚያደርግ አስረድቷል፡፡

የስፖርት ማዛውተሪያ ስፍራዎች ከመስራት በተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ብሪሞ ሜዳ እንደሚጠቀም የሚገልጸው ወጣት ቢኒያም ምንዳዬ እንደሚለው እንደዚህ አይነት ንጽህና ያላቸውና ደረጃቸውን በጠበቁ መጫዎቻ ሜዳዎች የመዲናዋ ወጣቶች በሚኖሩበት፣ በሚማሩበትና በሚሰሩበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ትልቅ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

አያይዞም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ያለ ገደብ ህብረተሰቡ በተፈለገው ግዜ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያከናውንባቸው መሆን ይኖርባቸዋል በማለት በቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች አብራርቷል፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ በቂ ቁጥጥር እንዲደረግላቸው፣ ወቅቱን የጠበቀ ዕድሳትና ጥገና እንዲደረግላቸው፤ የአጠቃቀም ስርዓት ቢዘረጋላቸው፣ የሰዓት አደላደልና መሰል ጉዳዮች መፍትሄ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ አብራርቷል፡፡

እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ስርዓት ሊዘረጋላቸው እንደሚገባው የተገነዘበው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በፍትሐዊነት ለመጠቀም ይረዳ ዘንድ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አስተዳደር ደንብ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ጽሑፍም የደንቡን ዋና ዋና ይዘቶች፣ የደንቡን አስፈላጊነትና እስካሁንስ ምን አይነት ችግሮችን እያቃለለ ነው? የሚሉትን ጉዳዮች እንዳስሳለን፡፡

በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አጠቃቀም ላይ የተዘጋጀውን ረቂቅ ደንብ ከመፅደቁ በፊት በከተማዋ  ከሚገኙ የስፖርት ምሁራን፣ ባለሙያዎች፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ ወጣቶች እና ነዋሪዎች ጋር ሰፊ ውይይት ስለመደረጉ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የህብረተሰቡን በተለይ የወጣቶች እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የዘወትር ጥያቄ የሆነውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ለመቅረፍ ከ5 ዓመት ወዲህ የተሰሩ ከ 1 ሺህ 300 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአግባቡ ለመጠቀም የወጣው ደንብ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚገልጹት ደግሞ በቢሮው የማዕከላትና ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አስተዳደር ልማት ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ ባዩ ናቸው፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እና የስፖርት ዓይነቶች ያካተቱ መሆናቸው ቀደም ሲል ከነበሩት የተለዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ይህም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንዲሁም ጤናው የተጠበቀ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲተዳደሩ ማድረግ አስፈላጊ ስለመሆኑ ታምኖበት ወደ ስራ ተገብቷል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለተሰሩበት ዓላማ ብቻ እንዲውሉ የሚያግዘው ደንብ በርካታ ግቦችን ለማሳካት እንደተዘጋጀ የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ አሁን ላይ ደግሞ በከተማዋ የሚገኙ 38 የስፖርት ፌዴሬሽኖችን ታሳቢ ያደረገ ዝርዝር መመሪያ ጭምር እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በመዲናዋ የሚገኙት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለሌላ ዓላማ እንዳይውሉ ጥበቃና ከለላ ማድረግ፣ ከህገ ወጥ ወረራ በመካላከል ደህንነታቸውን መጠበቅ፣ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩም በኋላ ባለሙያዎችን በመመደብ በአግባቡ ማስተዳደር ያስችላል ሲሉም የደንቡን ጠቀሜታ ያብራራሉ፡፡ አያይዘውም የሜዳ ተንከባካቢ፣ ጥበቃ እና የጽዳት ሰራተኞችን በመመደብ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ጥራት መጠበቅ ያስችላል ብለዋለ፡፡

እነዚህ ከተማዋን እንዲመጥኑ ተደርገው የተሰሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሁል ጊዜ በመንግስት በጀት መደገፍ ስለማይችሉም ራሳቸውን በገቢ እንዲችሉ ለማድረግ ገቢ የሚያመነጩበት አሰራርም በደንቡ ላይ ተካትቷል። ማዘውተሪያ ስፍራዎቹን በዘላቂነት ለመጠቀም እንዲያስችል አነስተኛ ክፍያ እንዲከፈልባቸውና ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ መጫወቻ ሜዳዎች ዙሪያም የተለያዩ ሱቆችን በመክፈት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹን በገቢ እንዲደግፉ እየተደረገ ስለመሆኑ ሰምተናል፡፡

በሌላም በኩል በመዲናዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ከትምህርት ሰዓት ውጪ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡበት አሰራር የተዘረጋ ሲሆን፣ ለዚህም ከትምህርት ቢሮ ጋር በተደረሰ ስምምነት ስፍራዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በኩል አስፈላጊው እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ፡፡

የአዲስ ተስፋችን እግር ኳስ ፕሮጀክት መስራችና አሰልጣኝ መሀመድ ናስር ከስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በሰጡን አሰተያየት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቅሰዋል። ከስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በተጨማሪ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችና በትምህርት ቤቶች የሚገኙ መጫወቻ ሜዳዎች ጭምር ለውድድር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ዘወትር ለአገልግሎት ክፍት ሊሆኑ እና ደረጃቸው ሊሻሻል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

እንደ አሰልጣኝ መሀመድ ማብራሪያ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው በማድረግ ከመንግስት ድጎማ ተላቅቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ይገባል፡፡ ተቋማቱ በባለሙያ እንዲተዳደሩ ቢደረግ፣ በአንዳንዶቹ ላይ ከመጫወቻ ሜዳ ውጪ እንደ መጸዳጃ ቤትና ፍሳሽ ማስወገጃ፣ ልብስ መቀየሪያና መሰል ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አንስተው ነበር። እንደዚሁም ሜዳዎቹ በተለይ ለአዳጊ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠቅሰው ነበር፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲተዳደሩበት የወጣውን ደንብ ጠቅሰው ሀሰባቸውን ያካፈሉን አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት ቦታዎቹ በህግ እንዲተዳደሩ መደረጋቸው ለእነዚህ ችግሮች ሁሉ እልባት ይሰጣል፡፡

ለእግሮቻቸው ምቹ ባልሆኑ ሜዳዎችና ከባዶ እግር ያልተናነሱ ጫማዎች ተጫምተው እግር ኳስን ጨምሮ ልዩ ልዩ ስፖርቶች በፍቅር የሚዘወተርባት ከተማ ወጣቶች ለዓመታት ያነሱት የነበረው ጥያቄዎችም ምላሽ አግኝተዋል፡፡ በመዲናዋ የሚገኙ ሜዳዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው ሳያንስ እየፈረሱ ለሌላ ዓላማ ይውሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ማንኛውም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ለህዝብ ጥቅም ተብሎ በልማት ሲነሳ ምትክ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው ደንቡ ያስገድዳል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተሰርተው ለወጣቶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የመጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ቁጥር ወደ 5 ሺህ ለማድረስ ዕቅድ ይዞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review