AMN- መጋቢት 1/2017 ዓ.ም
በሶማሌ እና አፋር ወንድም ህዝቦች መካከል የተጀመረውን ሰላም ዘላቂ የማድረግ ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ።
የሶማሌ እና አፋር ወንድም ህዝብ “ኢፍጣር ለአብሮነት እና ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ የጋራ የኢፍጣር ፕሮግራም በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እንዳሉት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ በርካታ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተለይ የለውጡ መንግስት እውነተኛ ፌዴራሊዝምን መገንባት የሚያስችሉ ተግባራዊ ስራዎች ማከናወን ችሏል ብለዋል።
አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በፌዴራል መንግስት፤ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሌሎች አካላት ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተለይ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን የመቅረፍና ዘላቂ ሰላምን የማጎልበት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ዘላቂ እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በህዝቦች መካከል የተጀመረውን ሰላምን ዘላቂ የማድረግ ስራ ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
በተለይ በመቀራረብ፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ገልጸው በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው አንድነትና ትስስርም እንደሚጠናከር አስታውቀዋል።
የጋራ ህልምና ራዕይ ያላቸው ህዝቦች ተደጋግፈው ማደግ አለባቸው ያሉት ደግሞ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ናቸው።
በአካባቢው አጋጥሞ የነበረው የሰላም እጦት ህዝቡን ለችግር መዳረጉን ጠቁመው የዛሬው ቀን የአብሮነት ማብሰሪያ ቀን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በግጭቱ የተጎዱትን የመካስና የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው የመመለስ ተግባር ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ረመዳን የተለየ የእዝነትና የራህመት ወር በመሆኑ በወንድማማች ህዝቦች መካከል ሰላም መጠናከሩ ትልቅ ድል ነው ብለዋል።
ቀኑም እርቅና ሰላም የወረደበት እለትና የፈጣሪም ምህረት የተገኘበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለዚህ በጎ ነገር አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቀጣይም በአፋር ክልል ተመሳሳይ ፕሮግራም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።