በሶማሌ ክልል ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በእርሻ የሚለማው መሬት በሦስት እጥፍ አድጓል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በሶማሌ ክልል ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በእርሻ የሚለማው መሬት በሦስት እጥፍ አድጓል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN-ታህሣሥ 25/2017 ዓ.ም

በሶማሌ ክልል በእርሻ ይለማ የነበረው 350 ሺ ሄክታር መሬት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሦስት እጥፍ በማሳደግ ከ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት እየለማ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣የሶማሌ ክልል ማደግና መበልጸግ ኢትዮጵያንና ምስራቅ አፍሪካን መመገብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ግጭት አያስፈልግም፣ ተረጋግተን ተወያይተን በተደመረ መንፈስ የጀመርነውን የልማት ስራ ማጠናከር ይኖርብናል” ሲሉም አክለዋል፡፡

ሶማሌ ከለማ ኢትዮጵያ ትለማለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልሉ ካልለማና በእርዳታ የሚቆይ ከሆነ ኢትዮጵያም በአጠቃላይ በድህነት ትቆያለች ብለዋል፡፡

“የእኛ ፍላጎት የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት ነው፣ ለዚህ ደግሞ ሸበሌ ብቻ ሳይሆን በርካታ ወንዞች አሉን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ መሬት እና የከርሰምድር ሀብት እንዲሁም ትጉህ የሆኑ አርብቶ አደሮች እንደሚገኙ በማውሳት ጠንካራ አመራር ከተሰጠ የሶማሌ ክልል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ህዝቦችም በረከት መሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ሙሉ ትኩረታችን ልማት ብቻ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡ በክልሉ በርካታ መንገዶች እና ከተሞች እየተሰሩና እየለሙ መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ በእርሻ ይለማ የነበረው 350 ሺ ሄክታር መሬት ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አሁን ላይ በሦስት እጥፍ አድጎ ከ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ክልሉ 2 እና 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው መሆኑን በማውሳት ይህ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ለማኝ ሳትሆን ረጂ፣ የጭቅጭቅና ጦርነት ምድር ሳትሆን የሰላም ምድር እንድትሆን ሁላችንም በተባበረ ክንድ በተደመረ መንፈስ አብረን እንስራ” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review