AMN-ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም
የፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለማስተግበር በተዘጋጁ ረቂቅ የህግ ማእቀፎች ዙሪያ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ሥላሴ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበባ እምቢያለ፣ የአህጉራዊው የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፖል-ሲሞን ሀንዲ እንዲሁም የዘርፉ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለማስተግበር የተዘጋጁ ረቂቅ የህግ ማእቀፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል።
የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ሥላሴ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አሳታፊ መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬው መድረክ ለፖሊሲው ትግበራ አጋዥ ሀሳቦች የሚገኙበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበባ እምቢያለ፥ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ግልፅ በሆነ መንገድ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
መድረኩ የሽግግር ፍትህ ዓላማዎችን ለማሳካት የተነደፈ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአህጉራዊው የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፖል-ሲሞን ሀንዲ የሽግግር ፍትሕ ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር የወሰደችውን ቁርጠኝነት ያደነቁት ዳይሬክተሩ፥ የዛሬው መድረክ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡