በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በደሴ ከተማ የተገነባ ዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ ምርቱን ማከፋፈል ጀመረ

You are currently viewing በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በደሴ ከተማ የተገነባ ዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ ምርቱን ማከፋፈል ጀመረ

AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም

በደሴ ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው ዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ ምርቱን ማከፋፈል ጀምሯል።

ፋብሪካው የዳቦ ምርቱን በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተዘጋጁ የዳቦ መሸጫ ማዕከላት ዛሬ ማከፋፈል ጀምሯል፡፡

የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የከተማውን ሰላም ከመጠበቅ በተጓዳኝ የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡

በዚህም በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ በየክፍለ ከተማው የዳቦ መሸጫ ማዕከላት ተመቻችተው የማከፋፈል ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ፋብሪካው ምርቱን በብዛትና በጥራት እያመረተ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ የከተማ አስተዳደሩ 30 ሚሊዮን ብር በመመደብ የዳቦ መሸጫ ማዕከል፣ ግብዓትና የሰው ኃይል ማሟላቱን ገልጸዋል፡፡

የደሴ ዱቄትና ዳቦ ፋበሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት ፋብሪካው ጥራት ያለው ዳቦ እያመረተ በ30 መሸጫ ማዕከላት ለህብረተሰቡ ማቅረብ ጀምሯል፡፡

ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ዳቦና 420 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህም የአቅርቦት ክፍተቱን በመሙላት ገበያውን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና ያበረክታል ብልዋል፡፡

ፋብሪካው እያመረተ ያለውን ዱቄት ለግብዓት ከመጠቀም ባለፋ በተለያየ መጠን አሽጎ ለማህበረሰቡ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በጊዜያዊነት ለ38 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ለ170 ሰዎች የስራ እድሉን እንደሚፈጥር መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review