በበጀት ዓመቱ በመንግሥት እና በበጎ አድራጎት በአጠቃላይ ከ18 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለሕዝብ አገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በበጀት ዓመቱ በመንግሥት እና በበጎ አድራጎት በአጠቃላይ ከ18 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለሕዝብ አገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሐምሌ 10/2016 ዓ.ም

በ2016 በጀት ዓመት በመንግሥት እና በበጎ አድራጎት በአጠቃላይ 18 ሺህ 91 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለሕዝብ አገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ገለጹ።

ከነዚህም ውስጥ የሀገሪቱን እና የከተማዋን ገፅታ ከፍ ያደረጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የዓደዋ ድል መታሰቢያ፣ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል፣ የቃሊቲ – ቱሉዲምቱ – ቂሊንጦ መንገድ ተሻጋሪ ድልድዮች፣ 3 ግዙፍ የገበያ ማዕከላት እና የጉለሌ የተቀናጀ ልማትን ለአብነት አንሥተዋል።

የአቃቂ ግብርና ምርት እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የገበያ ማዕከል ተጠናቅቆ ሥራ መጀመሩን በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።

እንዱሁም 443 የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በዲዛይን እና ግንባታ ቢሮ ተገንብተዋል ብለዋል።

በከተማዋ ተጨማሪ ሆስፒታሎች ግንባታቸው እየተፋጠነ መሆኑን ጠቁመው፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ሆስፒታል 520 ክፍሎች እና 370 አልጋዎች ያሉት ግንባታው 58% መድረሱን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በኮልፌ ቀራኒዮ ከ520 በላይ ክፍሎች እና 423 አልጋዎች ያሉት ዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ 68% እንደደረሰ እና የጥሩነሽ ቤጂንግ እና የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ እንደቅደም ተከተላቸው 63% እና 54% ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ሌሎች በውጭ ምንዛሪ ችግር፣ በተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ በግብዓት አቅርቦት የገበያ ዋጋ መናር ምክንያት በዕቅዳቸው መሠረት በፍጥነት ያልሄዱ የትራንስፖርት ቢሮ ሕንፃ ግንባታን 67.2%፣ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ግንባታ 75.66%፣ እንዲሁም የየካ 2 መኪና ማቆሚያ ግንባታ፡ የአቃቂ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ፕሮጀክት ግንባታ ከነበረበት 86.8% ላይ እንደሚገኝ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።

በዮናስ በድሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review