AMN- መስከረም 22/2017 ዓ.ም
በቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ በ2016/2017 የምርት ዘመን ከ6 ሺህ 501 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ሰብል ማልማት መቻሉን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
አቶ ሽመልስ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በትኩረት ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አንዱ የጋራ አቅምን በአግባቡ መጠቀም ነው ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ሊቆጠሩ ከሚችሉ ስኬቶች መካከል ተደብቀው የቆዩ የህዝቡ ነባር እሴቶች ህጋዊ መሰረት ኖሯቸው እንዲተገበሩ መደረጉ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
ህጋዊ መሰረት እንዲኖራቸው ከተደረጉ መልካም እሴቶች መካከል አንዱ ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያን ጠቅሰው፤ ድርጅቱ በሶስት ዓመት ውስጥ 24 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባላትን በማፍራት እየተጠናከረ መጥቷል ነው ያሉት።
ቡሳ ጎኖፋ በቀዳሚነት የህዝቡን ነባር የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል በመመለስ በሰው ስራሽና በተፈጥሮ አዳጋ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም ቢሆንም ከዚህ ባለፈ መልኩ ህዝቡን ለመጥቅም ጊዜ አልወሰደበትም ብለዋል።
ቡሳ ጎኖፋ በአንድ ጎኑ የስራ ባህልን ማጠናከር፣ ተረጂነትን መቀነስና ራስን መቻል እያበረታታ ሲሆን በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን ለ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ማቅረብ ችሏል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህም በትምህርት ዘርፍ በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ለማፍራት የሚያግዝ ሲሆን በራሱ ባህልና እሴት የሚኮራ ህዝብ እንዲኖርም አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በቡሳ ጎኖፋ የልዩነት አስተሳሰቦች እየተፈቱ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ድርጅቱ ከአባላት ሀብት ከማሰበሰብ ጎን ለጎን በራሱ አቅም ወደ ምርታማነት ገብቷልም ብለዋል።
በዚሁ መሰረት በ2016/2017 ምርት ዘመን በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የግብርና ልማት ስራ እንዲያከናውን በተሰጠው አቅጣጫ በ6 ሺህ 501 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ሰብል እያላማ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም በድርጅቱ በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ ስራዎች ወደ ሁሉም ቀበሌዎች ማስፋፋት እንደሚገባም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።