AMN – ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም
በተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ ያለው በመሬት ውስጥ ያለው የማግማ( ቅልጥ አለት) እንቅስቃሴ ኃይል ባለመቆሙ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ-ፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ኤልያስ ሌዊ (ዶ/ር) ገለጹ።
በመሬት መንቀጥቀጥ (ንዝረት)፣ የመሬት መሰንጠቅ፣ የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታ፣ ሱናሚ፣ የመሬት መንሸራተትና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች አገራት ሲፈተኑ ይስተዋላል።
የእነዚህን አደጋዎች ክስተት ቀድሞ በመተንበይ ለመከላከል የሚደረግ ጥረት ቢኖርም እምብዛም የተሳካ አለመሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
በተለይም የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለመተንበይና ቀድሞ ለመከላከል አዳጋች መሆኑ ይነሳል።
የመሬት መንቀጥቀጥ በመሬት ውስጥ አለቶች ግጭት ሲፈጥሩ ወይም ሲላቀቁ በሚፈጠረው ክፍተት ከፍተኛ ድምፅ ሲገባ የሚከሰት ድንገተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ንዝረት ነው።
በዚህም ከፍተኛ መንቀጥቀጥ ሲያጋጥም የመሬት መናድ፣ የህንፃዎች መፈራረስ እና ሌሎችም ተያያዥ አደጋዎች የሚያስከትል በመሆኑ የህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ሊደርስ ይችላል።
በአፋር ክልል በተለይ ባለፉት ሳምንታት በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ በተለይም በአዲስ አበባና አካባቢው የተወሰኑ ሥፍራዎች በአጎራባች ከተሞች የመሬት ንዝረት ተሰምቷል።
ከዚህ ቀደም ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም እሁድ ጠዋት በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 9 የተመዘገበበት መሆኑ ይታወሳል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ለሦስተኛ ጊዜ ትናንትም በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ተከስቶ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 6 አካባቢ የተመዘገበበት ሲሆን፤ ንዝረቱ በአዲስ አበባና አካባቢው ተሰምቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ-ፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ኤልያስ ሌዊ (ዶ/ር)፤ በአዋሽ ፈንታሌና በአዲስ አበባ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝርት ለሦስተኛ ጊዜ ትናንት ምሽት ዳግም መከሰቱን አረጋግጠዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ የመከሰቱ ምክንያት በመሬት ውስጥ ያለው የማግማ እንቅስቃሴ ፈጣን (አክቲቭ) በመሆኑ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ በዚህ ወቅት ይከሰታል ወይም ይቆማል ብሎ መተንበይ አዳጋች መሆኑን አንስተው፤ በመሬት ውስጥ ያለው የማግም እንቅስቃሴ ሲያቆም አብሮ የሚቆም ይሆናል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ-ፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ በጉዳዩ ዙሪያ ወቅታዊ መረጃዎችን በማደራጀትና ተደራሽ በማድረግ እየሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ ንዝረት ሲያጋጥም ለአደጋ ከሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች መታቀብ በተረጋጋ ሁኔታ ለማሳለፍ መሞከር ተገቢ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በዓለም ላይ እስካሁን ካጋጠሙት የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች መካከል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1960 በቺሊ የተከሰተውና በሬክተር ስኬል 9 ነጥብ 5 ሆኖ የተመዘገበውና ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።