መጋቢት 7/2017 ዓ.ም
በ2017 ዓ.ም 107 ሺ ወይም ከ31ሺ በላይ አባዎራዎች ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሞላ ለኤኤምኤን ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
የከተማ ልማት እና ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሚገኙ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡
በፕሮጀክቱ የሚካተቱ ዜጎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የልየታ ሥራወ በጥንቃቄ እንደሚከናወን ነው አቶ ሰለሞን የገለፁት፡፡
እነዚህ ዜጎች ለሶስት አመት በሚቆየው ፕሮግራም ውስጥ ተካተው የአመለካከት ለውጥ፣ የህይወት ክህሎት፣ የገንዘብ አያያዝ፣ ቁጠባ፣ ሠርቶ መለወጥ፣ ቤተሰብ አስተዳደግ፣ አመጋገብ ሥርዓት እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ይሠጣቸዋል፡፡
ሥልጠናውን ሲያጠናቅቁ በመረጡት የሥራ ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ የሚያስችል ቴክኒካዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ከሚሰሩት የአካባቢ ልማት ሥራ ከሚያገኙት ገቢ ላይ 20 በመቶ ይቆጥባሉ ብለዋል፡፡
ቁጠባቸውን መሠረት በማድረግም በአንድ ቤተሰብ ደረጃ 600 ዶላር ድጋፍ አግኝተው ወደ መረጡት ዘርፍ በቀጥታ እንደሚገቡ ነው ያስረዱት፡፡
ዜጎች በዘላቂነት ተረጂ እንዲሆኑ ሳይሆን በዘላቂነት አምራች ሆነው ለራሳቸው እና ለሀገራቸው እድገት አስዋፅዖ እንዲያበረክቱ ነው መንግስት በትኩረት የሚሰራውም ብለዋል፡፡
በተሠራው ሥራም በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ2009 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ 415ሺ 923 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የነበሩ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ሆነዋል ፡፡ እነዚህ የድጋፉ ተጠቃሚ ዜጎች ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው፣ አረጋዊያን ፣ በአንድ ወቅት የሀገር ባለ ውለታ የነበሩ እና አሁን ላይ በህመም ወይም በሌሎች ምክንያቶች መሥራት ያልቻሉ እና መሥራት እየቻሉ ደግሞ ሰርተው ለመለወጥ እድሉን ያላገኙ እና በድህነት ውስጥ የነበሩ ዜጎች መሆናቸውን አስገዝበዋል፡፡
በተያዘው 2017 ዓ.ም “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው ንቅናቄ 128 ሺ 344 ዜጎች ወይም በአባ ዎራ ደረጃ 37ሺ የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን በ2017/18 ዓ.ም ለማስመረቅ እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ታሕሳስ 27 ቀን 2017 ዓ.ም 107 ሺ ወይም በአባ ወራ ደረጃ 31ሺ 2 ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር ማስመረቅ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
እነዚህ ዜጎች በአሁኑ ወቅት ከጉልት ሥራ ጀምሮ የህጻናት ማቆያ በማቋቋም እና በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተው ሌላ ሰው እስከ መቅጥር መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ99 በመቶ በላይ የሚሆኑት እራሳቸውን ችለው ውጤታማ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ከደረሱበት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ደረጃ ወደ ኋላ እንዳይመለሱ መንግስት ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
በቀጣይ 2018 በጀት አመትም 19ሺ ወይም 6ሺ 999 አባ ወራዎች እንደሚመረቁ ገልፀዋል፡፡ ለነዚህ ተጠቃሚዎች ከአንድ ወር በፊት 348 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ በመንግስት በኩል የተለቀቀ ሲሆን 70 በመቶ ተጠቃሚዎችም ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል፡፡
ተረጂነት አስተሳሰብ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ይህን አስተሳሰብ የመቀየር ሥራ በመንግስት በኩል በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ 154ሺ 923 ተጠቃሚዎች በፅዳት፣ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገገድ፣ ውበት እና አረንጓዴ ልማት፣ አፈር እና ውሃ ጥበቃ (ተፋሰስ)፣ ለከተማ ግብርና ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና አነስተኛ የመሠረተ ልማት ሥራ ላይ በመሳተፍ ከሚያገኙት ገቢ እየቆጠቡ መንግስት በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ወደ ቀጣይ የህይወት ምዕራፍ ይሸገጋራሉ ብለዋል፡፡
ድጋፍ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ይህ ሊሆን የቻለው ሁል ጊዜ የለጋሽ ሀገራትን እጅ እየጠበቅን መለወጥ የማቻይል በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
በማሬ ቃጦ