በቴክኖሎጂ የተደገፈው የገቢ አሰባሰብ ምን ውጤት አስገኘ?

በቴክኖሎጂ የተደገፈው የገቢ አሰባሰብ ምን ውጤት አስገኘ?

አቶ ሀይሌ ቶማስ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ነዋሪ ናቸው፡፡ የወጥ ቤት ዕቃዎች ንግድ ላይ የተሰማሩ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ ሲሆኑ በየዓመቱ የሐምሌ ወር ሲመጣ የሚጠበቅባቸውን ግብር ለመክፈል ወደ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ያቀናሉ፡፡ ሆኖም ያገኙት የነበረው አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ አልነበረም፡፡ ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ሰልፍና መጨናነቅ ያጋጥማቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አገልግሎቱ በወረቀት የሚሰጥና የዘመነ ስላልነበር ወረፋ ጠብቀው፣ አንዳንድ ጊዜም እስከ ሶስት ቀን ድረስ ተመላልሰው ነበር ግብራቸውን የሚከፍሉት፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተግባራዊ እየሆነ ያለው በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ወደ ፅህፈት ቤቱ በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው በስልካቸው የግብር መጠን ተጠቅሶ ይላክላቸዋል፤ በባንክ በኩልም  ይከፍላሉ፡፡ በዚህ መንገድ እስከአሁን ለሁለት ጊዜ ያህል እንደከፈሉ የሚናገሩት አቶ ሀይሌ፣ ይህም አገልግሎት ለማግኘት ያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት አስቀርቶላቸዋል፡፡ “ጊዜዬን ቆጥቦልኛል፤ ክፍያውም ጥሬ ገንዘብ መያዝ ሳያስፈልግ ከባንክ ወደ ባንክ በማስተላለፍ የሚፈፀም ነው፡፡ አሰራሩ ቀላል ነው፡፡ በጣም ጥሩ ለውጥ ነው” ሲሉ ቴክኖሎጂን በማስደገፍ እየተሰጠ ስላለው አገልግሎት ያላቸውን ሀሳብ አጋርተውናል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ነዋሪ የሆኑትና በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ መስፍን ፀጋዬ እንዲሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ገቢዎች ጽህፈት ቤት መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ቦታ ሆነው ግብራቸውን እየከፈሉ እንደሚገኙ ይናገራሉ። የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ መሆናቸውን የነገሩን አቶ መስፍን፣ በየዓመቱ የሐምሌ ወር ግብራቸውን ለመክፈል ወደ ገቢዎች ፅህፈት ቤት ሲሄዱ ከፍተኛ ወረፋ ያጋጥማቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜ  ከጠዋት እስከ ማታ ተሰልፈው ውለው፣ ምንም አይነት አገልግሎት ሳያገኙ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር፡፡

ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን የሚጠበቅባቸው የክፍያ መጠን በስልክ እየተላከላቸው የሚመጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ ስራ ላይ ሆነው በቀላሉ በቴሌ ብር አማካኝነት ክፍያ እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ አይነቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈው አሰራርም ግብር ለመክፈል ያጠፉት የነበረውን ጊዜና አላስፈላጊ እንግልት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ፤  1 ሺህ 739 የሚሆኑ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ይገኛሉ፡፡ በፅህፈት ቤቱ ተገልጋዮች ወደ ገቢዎች ፅህፈት ቤት በአካል መምጣት ሳይጠበቅባቸው፣ የሚከፍሉት የግብር መጠን ተወስኖ በስልክ እየተላከ ባሉበት ሆነው መክፈል የሚችሉበት በቴክኖሎጂ የተደገፈው የገቢ አሰባሰብ (ኢቲታክስ) ስርዓት ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህም ተገልጋዮችን ከአላስፈላጊ እንግልትና ወረፋ፣ ባለሙያዎች ላይም የሚፈጠረውን መጨናነቅና ጫና በማስቀረት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ማስቻሉን የወረዳው ማይክሮ ግብር ከፋይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስካለ ግርማ ተናግረዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ለግብር ከፋዮች በኢ-ታክስ ቴክኖሎጂ አማካኝነት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል

በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በወረዳው የሚገኙ ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው የደረሳቸውን መረጃ መሰረት በማድረግ በቴሌ ብር፣ ሲቢኢ ብር አሊያም ባንክ በመሄድ ክፍያቸውን መፈፀም ችለዋል፡፡ አዲስ ወደ ንግድ ስርዓቱ የገቡ እና የአከራይ ተከራይ ግብር ለመክፈል የግድ መረጃዎችን ማሳየት ከሚጠበቅባቸው በስተቀር ሌሎች ግብር ከፋዮች ወደ ፅህፈቱ በአካል መምጣት አይጠበቅባቸውም፡፡  ሆኖም አንዳንድ ባንክ የመጠቀም ልምድ ወይም በስልክ የሚላክላቸውን መልእክት በመረዳት ለመክፈል እውቀት የሌላቸው ግብር ከፋዮች አሉ፡፡ እነዚህን በማስተማር ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተለይ በግብር ማሳወቂያ ወቅት ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ለሚቸገሩ ግብር ከፋዮች ባለሙያዎች ተመድበው እንዲደግፏቸው ይደረጋል። ከዚህም ባሻገር መድረኮችን በማዘጋጀትና በገፅ ለገፅ ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ 18 ሺህ 334 የደረጃ “ሐ”፣ 3 ሺህ 69 ደረጃ “ለ”፣ 4 ሺህ 777 የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ይገኛሉ፡፡ ለእነዚህ ተገልጋዮች የሚሰጡ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እየተሰጡ እንደሚገኝ የአራዳ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉ ኃይለሚካኤል ያብራራሉ፡፡

በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ግብር ከፋዮች መካከል ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ሲሆኑ፣ ከዚህ በፊት እነዚህ ግብር ከፋዮች፣ ግብራቸውን በሚከፍሉበት ወቅት በተለይ የመጨረሻ የግብር መክፈያ ቀናት ከፍተኛ ሰልፍና መጨናነቅ ይታይ ነበር፡፡ ወረፋ ለማስጠበቅ ፖሊስ ጭምር ተመድቦ ነበር አገልግሎት የሚሰጠው፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ግብር ከፋዮች ወደ ቢሮ ሳይመጡ ባሉበት ሆነው የሚከፍሉት የግብር መጠን በስልካቸው እንዲደርሳቸው፣ በባንክ ወይም በተለያዩ ኦንላይን የክፍያ አማራጭ እንዲከፍሉም እየተደረገ ይገኛል፡፡ የክረምት ወቅት እንደመሆኑ ድንኳን የተዘጋጀ ቢሆንም በተለይ ባለፈው ዓመት የግብር ማሳወቂያ ወቅት እንደበፊቱ ሰልፍ አልነበረም፡፡ ጥቂት ተገልጋዮች ብቻ ነበር በአካል የመጡት፡፡

ወይዘሮ ሙሉ እንደነገሩን፣ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ግብር ከፋዮች በኦንላይን መረጃቸውን በማስገባት የሚያሳውቁበትና የሚከፍሉበት የኢ- ፋይሊንግ (ኤሌክትሮኒክስ ፋይሊንግ) እና ኢ- ፔይመንት (ኤሌክትሮኒከስ ፔይመንት) አሰራር ባለፈው ዓመት ተጀምሯል፡፡ ይህንን አሰራር በአራዳ ክፍለ ከተማ በደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ለመጀመር 50 ግብር ከፋዮችን በመለየት ወደዚህ ስርዓት ለማስገባት ለባለሙያዎች እና ግብር ከፋዮችም በአጠቃቀሙ ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ሌላኛው ቅኝት ያደረግንበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ነው፡፡ በጽህፈት ቤቱ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ያላቸው ግብር ከፋዮች ይስተናገዳሉ፡፡ ከአማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እንዲገለገሉበት የተዘረጋው ቴክኖሎጂ (ኢ-ፋይሊንግ) አጠቃቀም ዙሪያ የቴክኒክ ድጋፍ ለመጠየቅ ወደ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ እንደመጡ የነገሩን አቶ ጀማል ሁሴን ድርጅቱ ረጅም ዓመታት ግብር ሲከፍል መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በርካታ ሰነዶችን ተሸክመን እየመጣን ወረፋ ጠብቀን እስከ ሶስት ቀን ድረስ እየተመላለስን ነበር ግብራችንን የምንከፍለው። አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ተደግፎ መሰጠት ከጀመረ ወዲህ መጉላላት፣  በቀጠሮ “ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ኑ” የሚባለው ቀርቷል፡፡ ቢሯችን ቁጭ ብለን በማንኛውም ጊዜ የሚጠበቅብንን ታክስ ማሳወቅ፤ ክፍያውን፣ አስፈላጊውን መረጃም ወደ ሲስተም አስገብተን ከላክን በኋላ የሚመጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ እንከፍላለን፡፡ ከፍ ያለ ችግር ካላጋጠመን በስተቀር ወደ ተቋሙ የምንመጣበት ሁኔታ የለም፡፡ ትልቅ እፎይታን ሰጥቶናል፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ገንዘብ ወደ ባንክ ካስገባን በኋላ ወደ ገቢዎች የሂሳብ ቁጥር በቶሎ የማይገባበት ሁኔታ ያጋጥማል። በዚህ ምክንያት የመክፈያ ጊዜ አልፎ የተቀጣንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ባንኮች ዘንድ ስንጠይቅ በሲስተም ችግር ምክንያት እንደሆነ ነው የሚነግሩን፡፡ ከዚህ አንጻር ከሲስተም ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቀረፍ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ወይዘሮ ሚስጢረ ሀሰን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የኢ- ፋይሊንግ ክፍል ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፣ በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ 790 የሚሆኑ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች አገልግሎት እያገኙ ይገኛሉ፡፡

ለተገልጋዮች የሚሰጠው አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ከሁለት ዓመት ወዲህ ጀምሮ ግብር ከፋዮች በኦንላይን በየትኛውም ቦታ ሆነው ግብር ለማሳወቅ መረጃዎችን የሚልኩበት ኢ- ፋይሊንግ የተሰኘ ስርዓት ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እንደመሆናቸው ግብራቸውን ለማሳወቅ ሲመጡ የሚይዙት መረጃ ማለትም ደረሰኞች፣ ፋይሎች በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ አንድ ግብር ከፋይ በሺህ የሚቆጠር ደረሰኝ ያለው እስከ ሃያ የሚደርስ የፋይል መያዣ (Box file) በመኪና ጭኖ ነበር ይመጣ ነበር ሲሉ ወይዘሮ ሚስጢረ ያስታውሳሉ፡፡

አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ከተደረገ ወዲህ ግብር ከፋዮች መረጃዎቻቸውን ተሸክመው መምጣት ሳይጠበቅባቸው ቢሮ ወይም ባሉበት ቦታ ሆነው መላክ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሙሉ በሙሉ ኢ- ፋይሊንግን  እየተጠቀሙ ይገኛል፡፡

ግብር ከፋዮች መረጃቸውን በሲስተም ካስገቡ በኋላ ቀጥሎ ያለው ሂደት ክፍያውን በኢ- ፔይመንት ስርዓት መፈፀም ነው፡፡ የኢ- ፔይመንት ስርዓት ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ክፍያቸውን የሚከፍሉበት ስርዓት ሲሆን፣ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ባንክ ካስገቡ  በኋላ እንደበፊቱ ደረሰኝ ለመውሰድ ወደ ተቋሙ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ወዲያውኑ መክፈላቸውን የሚያሳይ ደረሰኝ በኢ- ሜይል ይደርሳቸዋል፡፡ ይህ ስርዓት ምልልስ በመቀነስ ተገልጋዩ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ የገቢ ሂሳብ ማጠቃለያ ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ ንግስት አየለ ናቸው፡፡

የኢ-ፔይመንት ሲስተሙ ላይ የመቆራረጥ፣ ግብር ከፋዮች መረጃቸውን ካስገቡ በኋላ የሚከፍሉበትን የሰነድ ቁጥር ያለማሳየት ክፍተቶች እንደሚታዩ የጠቀሱት ወይዘሮ ንግስት፣ በዚህም ምክንያት ሁሉም ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሲስተሙን በመጠቀም ግብር እየከፈሉ አይደለም፡፡ አሁንም በእጅ (በማንዋል) ክፍያ የሚፈፅሙ ግብር ከፋዮች ስላሉ ሁሉም መጠቀም እንዲችሉ ተጨማሪ ስራዎች መስራት እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡

ቢሮው ምን ይላል?

በመዲናዋ የሚሰበሰበው ገቢ፣ የግብር ከፋዮች ቁጥር፣ ግብር የሚከፈልበት የገቢ አይነት በተለያየ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ለዝግጅት ክፍላችን ያስረዳሉ፡፡ በ2010 በጀት ዓመት 33 ቢሊዮን ብር የነበረው ገቢ፤ በ2015 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 109 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የግብር ከፋዩ ቁጥርም ከ460 ሺህ በላይ ሆኗል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ

ይህንን ያህል ግብር ከፋይ በተቀላጠፈ መንገድ ለማስተናገድ፣ የግብር አይነቶችን ለመተግበር፣ የሚታቀደውን ገቢ ለመሰብሰብ አዳዲስ የአገልግሎት አማራጮችን ማየት እንደሚያስፈልግ አቶ አደም  ይናገራሉ፡፡

የገቢ አሰባሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ በገቢዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ፈጣንና ግልፅነትን የተላበሱ ለማድረግ ያግዛል፡፡ በዚህ ረገድም ታክስና ግብርን ለመወሰን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡

አንደኛው በወረዳ ደረጃ የሚገኙ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ታክስ ለመወሰንና ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ የሚገኘው የኢ ታክስ ስርዓት ነው፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ከዚህ ቀደም የንግድ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ወደ ገቢዎች ፅህፈት ቤቶች በአካል በመሄድ ከዕዳ ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ (ክሊራንስ) መውሰድ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ዘመናዊው አሰራር ከተጀመረ ወዲህ ግን ክፍያቸውን ባሉበት ቦታ እንደከፈሉ በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው ክሊራንስ ያገኛሉ፡፡

አቶ አደም እንደገለፁት፣ በአዲስ አበባ ከ350 ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በሚያሳውቁበት ወቅት ይታይ የነበረውን ከፍተኛ ሰልፍና ወረፋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማስቀረት ተችሏል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙት ቁጥራቸው እየጨመሩ፣ በአተገባበሩ ላይም ግልፅነት እየተፈጠረ መጥቷል፡፡

ከዚህ ባለፈ የሂሳብ መዝገብ መያዝ የሚገደዱ፣ በየወሩ አሊያም በየሶስት ወር ወደ ገቢዎች ፅህፈት ቤቶች በመሄድ ሪፖርት ማድረግ ያለባቸው የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የሚሰጠውን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ አደም አንስተዋል፡፡ እነዚህ ግብር ከፋዮች መረጃቸውን ተሸክመው በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ግብራቸውን የሚያሳውቁበትና የሚከፍሉበት የኢ- ፋይሊንግና ኢ- ፔይመንት አሰራር በአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት በአስራ ስድስቱም የገቢዎች ቅርንጫፎች ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ መረጃዎችን በሲስተም ሲልኩ፣ ባለሙያዎች የተላከውን በማየት ግብረ መልስ ከሰጡ በኋላ በኦንላይ ክፍያ ይፈፅማሉ። ወደዚህ የኢ- ፋይሊንግ እና ኢ-ፔይመንት ስርዓት ውስጥ የሚገቡ እስከ 120 ሺህ የሚሆኑ የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች በከተማዋ ይገኛሉ፡፡

በከፍተኛ ግብር ከፋዮች የተጀመረው የኢ- ፋይሊንግ እና ኢ- ፔይመንት ሲስተም ጋር በተያያዘ፣ ግብር ከፋዮች ክፍያውን በባንክ ካስገቡ በኋላ መክፈላቸውን በቶሎ ያለማሳወቅ ችግር ያጋጥማል የሚለውን አስተያየት በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የገቢ ሂሳቦች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ታየ ማስረሻ ይጋሩታል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከንግድ ባንክ እና ሲስተሙን በዋናነት ከሚከታተለው ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በትብብር በመስራት ለውጦች መጥተዋል። በ2015 በጀት ዓመት በሚያዚያ ወር 517፣  ግንቦት ወር 487፣ በሰኔ 366 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ኢ- ፔይመንትን በመጠቀም ግብራቸውን ከፍለዋል፡፡ ሁሉም ግብር ከፋዮች በኢ- ፔይመንት ግብራቸውን እንዲከፍሉ መረጃ እንዲያሟላ የማድረግ እና ሲስተሙ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የገቢዎች ቢሮ ኃላፊው እንደገለፁት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈው አገልግሎት ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ፣ ግልፅነትን በመጨመር፣ የገቢዎች ቢሮ የያዘውን ዕቅድ በዘመነ መንገድ ለማሳካት ያግዛል፡፡ ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ሲያውሉት የነበረውን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ሌላ ምርታማነትን በሚያሳድጉ ስራዎች እንዲያውሉት ያደርጋል፤ በጥቅሉ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ ያግዛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በገቢዎች ቢሮ ስራ ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂዎች የሚሰበሰበውን ገቢ በማሳደግ ረገድ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ ግብር ከፋዮች ከግብር ውሳኔ በተጨማሪ የሚፈልጓቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የቅጥር ደመወዝ የሚከፍሉ ግብር ስለመክፈላቸው ማስረጃ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ የእነዚህን ተገልጋዮች ማህደራቸውን ከመዝገብ ቤት ፈልጎ ማውጣትና ውሳኔ መስጠት ጊዜ ይወስዳል፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል የፋይል ማኔጅመንት የተሰኘ ፓኬጅ በአስራ ስድስቱ የገቢዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ለመጀመር እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ያሉ ፋይሎች በሙሉ ስካን ተደርገው ተደራጅተው ሰርቨር ላይ የማስቀመጥና ተገልጋዩ ሲፈልግ በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል ነው፡፡ እስከአሁን ከ430 ሺህ በላይ ፋይሎች የተለዩ ሲሆን ስካን አድርጎ ለማስቀመጥ ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ተሞክሮ በመውሰድ ለመስራት ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ሌላው ቢሮው በተለያዩ ዘርፎች ማለትም አስራ ስድስት የገቢዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች፣ 32 የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት፣ 11 ክፍለ ከተሞች በጥቅሉ ወደ 60 አካባቢ ከሚደርሱ ተቋማት የገቢ ሪፖርት ይሰበስባል። ይህንንም ከወረቀት ነፃ በሆነ መንገድ ሪፖርት መቀባበል የሚቻልበት ኢ- ረቨኒው (E- Revenue) የተሰኘ ሲስተም እንዲበለፅግ መደረጉን አቶ አደም ነግረውናል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በ2016 በጀት ዓመት አስራ አንድ ወራት ውስጥ 133 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል። ገቢ ለከተማዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚኖረው አበርክቶ ትልቅ እንደመሆኑ መጠን ከዚህም በላይ እንዲያድግ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ የተገልጋዩን እርካታ ከማሳደግ ባለፈ ገቢውን ለመጨመርም አጋዥ ስለሆነ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review