“የወረቀት ካርታን ወደ ዲጂታል ካርታ ለማስቀየር በእጅ ስልኬ ነበር በሲስተም ያመለከትኩት፡፡ የመሬት አገልግሎቱ በዚህ ደረጃ በቴክኖሎጂ መሰጠቱ መልካም ነው፡፡ ግልፅነትን ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን ሶስት ወር ሆኖኛል፤ እስከአሁን ካርታውን አላገኘሁም፡፡ ብዙ ጊዜ ‘ሲስተም የለም’ ይባላል፡፡ መፍትሔ ይሰጠን” ይላሉ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሲገለገሉ ያገኘናቸው የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ነዋሪው አቶ ልዑል ጫኔ፡፡
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ) በበኩላቸው የወሰን ችካል አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጽህፈት ቤቱ ጎራ ቢሉም በሲስተም መቆራረጥ አገልግሎቱን በወቅቱ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የሚገልፁት፡፡ ከዚህ ሌላ በአንዳንድ ባለሙያዎች “የሻይ ቡና በሉ” የሚል ጥያቄ እንደሚነሳና ጉዳያቸው ሳይፈታ እንደዘገየባቸው ገልፀው፤ ችግሩን የሚመለከተው አካል እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 ነዋሪ ወይዘሮ ዘመን ማመጫን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሲገለገሉ ነው ያገኘናቸው፡፡ በጽህፈት ቤቱ የወሰን ችካል አገልግሎት በተገቢው ማግኘታቸውን ገልፀው፤ ነገር ግን የኢ-ካርታ (ዲጂታል ካርታ) አገልግሎት ለማግኘት በሄዱበት ወቅት “ሲስተም የለም” በሚል እንደተጉላሉና ችግሩም መፍትሔ የሚፈልግ እንደሆነ አንስተዋል።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 ነዋሪው አቶ ዘውዱ ሙሉጌታም አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ መሰጠቱ የተሻለ መሆኑን ገልፀው፤ የመሬት ካርታ ለማውጣት ቢሄዱም ሲስተም ባለመኖሩ አገልግሎቱን ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል የተገልጋዮችን አስተያየትና ቅሬታ በመያዝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የየካ እና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች አነጋግሯል፡፡ በጉዳዩ ላይም ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የየካ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ተገኝ በሰጡት ምላሽ፣ የመሬት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ መሰጠት የተጀመረው በ2017 በጀት ዓመት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ለአብነት የወሰን ችካል፣ የካሳ ክፍያ፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ኢ-ካርታ (Electronic land holding Certificate) ወይም ዲጂታል ካርታ፣ እዳ መሰረዝ እና አብዛኛው የመሬት አገልግሎቶች በሲስተም ተደግፈው እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ ሲጀመር 27 አገልግሎቶች በሲስተም ሲሰጥ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ወደ 40 የሚሆኑ የተለያዩ የመሬት አገልግሎቶች እየተሰጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

የመሬት አገልግሎት በሲስተም መሰጠት በመጀመሩ በአገልግሎቱ ላይ ለውጥ መታየቱንም ኃላፊው ይናገራሉ። የወረቀት ንክኪን አስቀርቷል፣ ስራዎችን ከወረቀት ወደ ዘመናዊ አሰራር
ቀይሯል። በተለይም ከዚህ ቀደም ባለጉዳይ አገልግሎት ለማግኘት ጠዋት 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ሰልፍ ይይዝ ነበር። አሁን ይህ ቀርቶ አንድ ባለጉዳይ ቤቱ ሆኖ የእጅ ስልኩን በመጠቀም በሲስተም ማመልከቻ የሚልክበት፤ የአገልግሎት ክፍያ በየትኛውም ቦታ በመሆን በቴሌ ብር ክፍያ የሚፈፅምበት እና በማንኛውም ሰዓት አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት አሰራር በመፈጠሩ የተገልጋይን እንግልት ቀንሷል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ወይም ኢ-ካርታ አገልግሎት ለማግኘት አልፎ አልፎ እስከ ሁለትና ሶስት ወራት እንደሚቆይ አንስተዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ላልናቸው ኃላፊው ሲመልሱ፤ “የመሬት አገልግሎት አሰጣጡ እንደተጀመረ አሰራሩ አዲስ በመሆኑ ከመላመድ አንፃርና የሲስተም መቆራረጥ ስለሚኖር ይህ ችግር ያጋጥም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የኢ-ካርታ አገልግሎት ተገልጋዩ በሲስተም ሲያመለክት በሚፈጥረው ስህተት ካልሆነ በስተቀር ሁለትና ሶስት ወራት አይቆይም፡፡ ተገልጋዩ በምዝገባ ወቅት ስህተት ከፈጠረ ሲስተሙ የስህተት ማረም (Error Correction) እስከሚሰራ ለወራት ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህን ለመቅረፍም ተገልጋዩ ሲያመለክት ስህተት እንዳይፈፅምና በወቅቱ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማድረግ ጽህፈት ቤቱ ሁለት ባለሙያዎች በመመደብ ድጋፍ የማድረግ ስራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም አገልግሎቱ በሲስተም ከተጀመረ በኋላ በዘጠኝ ወራት ወደ 3 ሺህ የሚሆን የኢ-ካርታ አገልግሎት ተሰጥቷል” ብለዋል፡፡
የልማት ተነሺ ተገልጋዮች በሲስተም መቆራረጥ ችግር የወሰን ችካል አገልግሎትን በወቅቱ ማግኘት እንዳልቻሉ እና በአንዳንድ ባለሙያዎች “የሻይ ቡና በሉን” የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተገልጋዮች ገልፀውልናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ መልካሙ በሰጡት ምላሽ፤ “የወሰን ችካል አገልግሎት በአግባቡ በሲስተም እየተሰጠ የሚገኝ ቢሆንም ሲስተም ላይ ባጋጠመ ችግር በአገልግሎቱ ላይ ክፍተት ሊፈጠር ችሏል፡፡ የሲስተም ችግሩ በቅርቡ የሚፈታ ይሆናል፡፡ በአንዳንድ ባለሙያዎች “የሻይ ቡና በሉ” የሚል ጥያቄ ተጠይቀናል ለተባለው እስካሁን “የእጅ መንሻ ጠየቁን” ተብሎ የደረሰን መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን አገልግሎቶች በሲስተም አማካኝነት የሚሰጡ በመሆኑ ይህ የመከሰት እድል አይኖረውም፡፡ አንድ ጉዳይ ከተገልጋይ ወደ ባለሙያ እጅ መቼ ደረሰ፣ ከደረሰ በኋላ ምን ያህል ጊዜ ቆየ፣ ባለሙያው በስራ ሂደት ተሳስቶም ከሆነ መሳሳቱን ሲስተሙ ራሱ ኦዲት ያደርገዋል፡፡ ሆኖም እጅ መንሻ በመጠየቅ አገልግሎትን የሚያጓትት ባለሙያ በትክክል በማስረጃ ተረጋግጦ ከተገኘ ይጠየቃል፡፡ በመመሪያው መሰረት ከስራና ከደመወዝ እስከመታገድ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ የመሬት አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ መሰጠት ከተጀመረ በኋላም ሲስተሙን ያለአግባብ የተጠቀሙ፣ ስራዎችን ያዘገዩ አምስት ባለሙያዎች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን አንድ ባለሙያ ከስራና ደመወዝ በማገድ በዲሲፕሊን እንዲጠየቅ ተደርጓል” ብለዋል፡፡

የመሬት አገልግሎትን ማዘመን ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት ወሳኝ አሰራር ነው የሚሉት አቶ መልካሙ “በቀጣይም ህብረተሰብን ማገልገል የህሊና እርካታን የሚሰጥ ተግባር መሆኑን ባለሙያዎች በመረዳት ተገልጋይን በማክበር ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አለባቸው፡፡ ህብረተሰቡም በአገልግሎቱ ላይ ቅሬታ ካለው በማንኛውም ሰዓት ረቡዕና ዓርብ የተገልጋይ ቀንን ጨምሮ ማሳወቅ አለበት” ሲሉም ኃላፊው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ ወይዘሮ ፍሬሰው ባዩ በተመሳሳይ በሰጡት ምላሽ፤ በጽህፈት ቤቱ የመሬት አገልግሎት በሲስተም መስጠት የተጀመረው በ2016 ዓ.ም ነው። 18 የመሬት አገልግሎቶች በሲስተም ይሰጣሉ፡፡ ለአብነት የካርታ ኮፒ፣ የወሰን ችካል፣ የስም ዝውውር እና የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ኢ-ካርታ) የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ተገልጋዮች የሚፈልጉትን አገልግሎት ቤታቸው ሆነው በሞባይል ስልካቸው ማግኘት ስለሚችሉ ጊዜያቸውን ለመቆጠብ አሰራሩ ተመራጭ ነው፡፡ ለአብነት በተያዘው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት አንድ ሺህ የኢ-ካርታ አገልግሎት እንደተሰጠ ገልፀዋል፡፡
የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ኢ-ካርታ (Electronic land holding Certificate) አገልግሎት ለማግኘት የሲስተም መቆራረጥ ችግር ለእንግልት እንደዳረጋቸው በተገልጋዮች ለተነሳው ጥያቄ ወ/ሮ ፍሬሰው በሰጡት ምላሽ፣ “ትክክል ነው፡፡ ኔትዎርክ ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ ስለምንጠቀም የሲስተም መቆራረጥ ችግር አጋጥሞናል፡፡ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን ለጽህፈት ቤቱ ለብቻው የኔትዎርክ ዝርጋታ ለማካሄድ ሰርቨር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ከአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተነጋገርን በመሆኑ ችግሩ ይፈታል” ብለዋል፡፡
በመሬት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ወይዘሮ ፍሬሰው፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት ስድስት ወራት የመሬት አገልግሎቱን በስታንዳርድ መሰረት በሲስተም ያልሰጡ፤ አገልግሎትን ያዘገዩና በዚህም ተገልጋይን ያጉላሉ 7 ባለሙያዎች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአግባቡ አገልግሎት የማይሰጡ ከተገኙ በመመሪያ መሰረት ከስራ እስከማሰናበትና በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ይሠራል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰጠው የመሬት አገልግሎት እያመጣ ያለውን ለውጥ አስመልክቶ የቢሮው የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ፈይሳ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል እንደገለጹት፤ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የመሬት አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ እንዲሁም ብልሹ አሰራርን ለመከላከል “ላንድ ቴንዩር ማኔጅመንት ሲስተም” የሚባል ሶፍትዌር ለምቶ ከ2016 ዓ.ም መጋቢት ወር ጀምሮ በማዕከልና በ11ዱም ክፍለ ከተሞች አገልግሎቱ በሲስተም ሙሉ በሙሉ መሰጠት ተጀምሯል፡፡
የመሬት አገልግሎቱ በሲስተም መሰጠት ከተጀመረ በኋላ ውጤት ማምጣቱንም አቶ ሀብታሙ ያነሳሉ። ይህም ከዚህ ቀደም በመዲናዋ ምን ያህል የተገልጋይ የይዞታ ማህደር አለ? የሚለው አይታወቅም ነበር፡፡ በሐሰተኛ መረጃ የይዞታ ባለቤት የሚሆኑም ነበሩ። በርካታ ሐሰተኛ የመሬት ሰነዶች ነበሩ፡፡ አሰራሩ ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነበር፡፡ አሁን ላይ አጠቃላይ የመሬት መረጃ ስካን ተደርጎ በሲስተም ገብቷል፡፡ በዚህም በሲስተም ላይ የይዞታ ማህደር ያለው ተገልጋይ ብቻ ነው አገልግሎቱን ማግኘት የሚችለው፡፡ ይህም ሐሰተኛ ሰነዶች እንዳይዘጋጁ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ ማጭበርበር እንዳይኖር ያደረገ አሰራር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም መረጃዎች ስካን እየተደረጉ ወደ ዲጂታል ተቀይረዋል። በዚህም 675 ሺህ 481 ባለይዞታዎች የወረቀት ማህደር እንዲሁም 47 ሺህ 153 የተለያዩ ዶክመንቶች ስካን ተደርገው በአጠቃላይ 722 ሺህ 634 በዲጂታል ተደራጅተዋል፡፡ ከ31 ሺህ በላይ የወረቀት ካርታ ወደ ዲጂታል የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ኢ-ካርታ) ተቀይሯል፡፡ ይህ ተግባር የሚቀጥል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በክፍለ ከተሞች ተገልጋዮች አልፎ አልፎ የሲስተም መቆራረጥ ችግር እንዳለ ያነሳሉ፡፡ ችግሩ ከምን የመነጨ ነው? ላልናቸው ኃላፊው ሲመልሱ፣ “የመሬት አገልግሎቱ ሲስተም ለምቶ አገልግሎቱ መሰጠት ከተጀመረ ገና አንድ ዓመት የሆነው ነው፡፡ በዚህም ቴክኖሎጂው አዳጊና በመልማት ላይ ያለ በመሆኑ አልፎ አልፎ የኔትዎርክ መቆራረጥ ያጋጥማል። ቴክኖሎጂው በሚፈልገው መሰረት ቴክኒካል ችግሮች እየታዩም እየተስተካከለ እየዳበረ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል መብራት ሲጠፋም ጀነሬተር እስከሚነሳ ኔትዎርክ ይቋረጣል፡፡ ይህ በአገልግሎቱ ላይ ክፍተት እየፈጠረ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ሆኖም የተከሰተው የሲስተም መቆራረጥ አሁን ተፈትቷል፡፡ በቀጣይም ችግሩን እያየን እየተስተካከለ እንዲሄድ በትኩረት እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል፡፡
የመሬት አገልግሎቱ ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የፀዳ እንዲሆን በትኩረት እየተሠራ ነው የሚሉት አቶ ሀብታሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 29 ባለሙያዎች እና ስምንት አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ከእነዚህ መካከል 24ቱ በክፍለ ከተሞች እና አምስቱ ደግሞ በማዕከል የሚሰሩ ናቸው። አመራሮቹ ከሀላፊነት እንዲነሱ ሲደረግ፤ በሌብነትና ብልሹ አሰራር ጥቆማ የቀረበባቸውና የተረጋገጠባቸው 18 ሰራተኞች ላይ የደመወዝ ቅጣትና የማስጠንቀቂያ እንዲሁም 11 ሰራተኞች ላይ ከስራ የማገድ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ በብልሹ አሰራር የተዘፈቁ ከተገኙ ተጠያቂ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሁለቱም ክፍለ ከተሞች በመገኘት ባደረገው ቅኝት የመሬት አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ መሰጠቱ የህብረተሰቡን እንግልት የቀነሰ መሆኑን ታዝበናል፡፡ ቀድሞ በተለይ አገልግሎት ለማግኘት ረዣዥም ሰልፍ መሰለፍ ግድ ነበር፡፡ አሁን ይህ አይስተዋልም፡፡ ተገልጋይ እንደመጣ ወደሚፈልገው ባለሙያ በመሄድ ሲስተናገድ ተመልክተናል፡፡ ሆኖም የሲስተም መቆራረጥ ችግር የበለጠ ህብረተሰቡን ለምሬት እንዳይዳርግ የሚመለከተው አካል በየጊዜው ክትትል ቢያደርግ አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳለጥ ያግዛል መልዕክታችን ነው፡፡
በሰገነት አስማማው