AMN- ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም
በቴክኖሎጂ የዳበረ ዜጋ ለመፍጠር በተማሪዎች ላይ መስራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ም/ቢሮ ሃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) አስገነዘቡ ፡፡
የአዲስ አበባ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የሚኒሚድያና የአይ ሲ ቲ ዲፓርትመንት ሃላፊዎች የኢትዮ-ኮደርስ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ነው።
በስልጠናው ላይ የአዲስ አበባ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ም/ቢሮ ሃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የሚገኙ የ2ኛ ደረጃና ከዚያ በላይ ያሉ ተማሪዎች ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያላቸው ዕድል ሰፊ በመሆኑ የ5ሚሊዮን ኮደር ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የስልጠናው አላማ ወጣቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችለው ክህሎት እንዲኖረው ማስቻል ነው ተብሏል ፡፡
መርሃ ግብሩ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የኦንላይን ኮርሶችን እና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ እ.ኤ.አ በ2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና አንድሮይድ ልማት መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎትን ለማስታጠቅን ያለመ ነውም ተብለዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር በአዲስ አበባ ከ2 ሺህ 300 በላይ ትምህርት ቤቶች ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ስላሉ የ2ኛ ደረጃና ከዚያ በላይ ያሉ ተማሪዎች የ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
ዛሬ እየሰለጠኑ የሚገኙ የሚኒሚድያና የአይ ሲ ቲ ዲፓርትመንት ሀላፊዎች በየትምህርት ቤታቸው ተማሪዎችን የመለየት ስራ እንዲሰሩ ይደረጋልም ብለዋል።
5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት የተነደፈ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መርሃ ግብር መሆኑ ይታወቃል ።
በሄለን ጀንበሬ