በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታየውን ብልሹ አሰራር ለማስቀረት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ እየተሰራ ነው፡- ትራንስፖርት ሚኒስቴር

You are currently viewing በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታየውን ብልሹ አሰራር ለማስቀረት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ እየተሰራ ነው፡- ትራንስፖርት ሚኒስቴር

AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም

በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታየውን ብልሹ አሰራር ለማስቀረት ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ ታግዞ መስራት እንደሚገባ የትራንስፖርት ሚንስትር ዴኤታ በርሆ ሀሰን ገለጹ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ሌሎች ስራዎችን በተመለከተ ክልሎች ልምድ የሚወስዱበት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታየውን ብልሹ አሰራርና የህዝብ እንግልትን ለማስቀረት ዘርፉን የማዘመንና ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያስታወቀው።

ሚኒስትር ዴኤታው የትራንስፖርት ዘርፉ የሀገር ኢኮኖሚ መሰረት እንደመሆኑ መጠን ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ አንስተዋል።

ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ ትራንስፖርት ዘርፍ እንደመሆኑ በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ላይ ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርግ ምቹና ዘመናዊ በሆነ መልኩ እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ የሚገኙ ተርሚናሎች፣ የፓርኪንግ ቦታዎች እና የብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎትን ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ያብባል ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መርሐ ግብር ላይ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የተለያዩ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ጉብኝት እንደሚደረግም ተጠቁሟል።

በመሀመድኑር አሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review