AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩን የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ሀሳብና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
ከወንጀልና ፖሊሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ እንደ አጠቃላይ በከተማ ደረጃ የወንጀል ምጣኔ መቀነሱን አመልክተዋል
ያም ሆኖ በከተማዋ ባሉ ተሸከርካሪዎች ተጠቅመው ከሚፈፀሙ የሿሿ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ፖሊስ ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ ተጠያቂ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ይህው ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ወንጀለኞችን ብቻ ሳይሆን ለወንጀል ተግባር የሚጠቀሙባቸውን ተሽከርካሪዎችና አከራዮቻቸውንም በሚዘጋጅ ደንብ ተጠያቂ ለማድረግ መታሰቡን አመልክተዋል ፡፡
በፖሊስ መዋቅር ውስጥ ያለው የሴቶች ተሳትፎን በተመለከተም ከምልመላ ጀምሮ በየደረጃው ባለው መዋቅር ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ባጠናው አዲስ መዋቅር ውስጥም የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል ኮሚሽነሩ ፡፡
ለሴት ፖሊስ አባላት የሚያገለግሉ የህፃናት ማቆያዎች በሁሉም ጣቢያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ያብራሩት ኮሚሽነር ጌቱ በቅርቡም የሚመረቁ የህፃናት ማቆያዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል ፡፡
በየደረጃው ያለው የፖሊስ መዋቅር የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ከማረጋገጥ አንፃር የተጣለበትን ህዝባዊ ሀላፊነት በሙሉ ቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ ያመለከቱት ኮሚሽነሩ የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ የሚያስቀምጣቸውን አቅጣጫዎች ተከትሎ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡
በሽመልስ ታደሰ