በትጋት የመጣ ውጤት፤ በብቃት የተሰጠ ሽልማት

አዲስ አበባ በለውጥ ምዕራፍ ላይ መሆኗን አለም እየመሰከረ ነው፡፡ ከተማዋ  እንደንስር እራሷን አድሳ እንደ ስሟም ውበትን ተላብሳ በርግጥም “አዲስ አበባ!” እየሆነች መምጣቷን መስካሪዎቿ ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በተለይ የኮሪደር ልማቱን ዋቢ በማድረግ የመዲናዋን መለወጥ የሚመሰክሩ በርክተዋል፡፡ መዲናዋን እንደ አዲስ የወለደው የኮሪደር ልማት፣ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የሕይወት መሻሻልን ታሳቢ ያደረጉ ብሎም ዘመኑን የዋጁ ስራዎቿ እንደ ሀገርም በተምሳሌትነት ተወስደው እየተሰራባቸው ስለመሆኑም ይታወቃል፡፡

ከሀገር አቀፍ ባሻገርም እንደ አህጉር፣ እንደ አለም አቀፍም በተምሳሌትነት እየተነሳ ያለው ይህ የመዲናዋ ለውጥ በከፍተኛ አመራሩ ብቃት እና በሁለንተናዊ ርብርብ መገኘቱን ታሳቢ በማድረግና የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አበርክቶ ትልቅ መሆኑን የተገነዘቡ አለም አቀፍ ተቋማትም የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክተውላቸዋል፡፡

ባሳለፍነው ሐሙስም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት ለማሻሻል ባሳዩት በሳል እና ቁርጠኛ አመራር በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የ‘ሴኡል ስማርት ሲቲ 2024’ የስማርት ሲቲ ባለ ራዕይ መሪ ሽልማትን አሸንፈዋል፡፡

ከንቲባዋ በዓለም ካሉ መሪዎች ከተማን ለመቀየር በትጋት በመሥራታቸው ልዩ እውቅና የሰጠው ውድድር በዓለም ዙሪያ ከ72 ሀገሮች እና ከ115 ከተሞች የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ያካተተ መሆኑም ተመላክቷል።

ሽልማቱ ዘላቂ፣ ለአካባቢ ተስማሚ፣ በቴክኖሎጂ የሚመራና ሁሉን አቀፍ ከተማ ለመፍጠር እንደ ኮሪደር ልማት ያሉ ትኩረት የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶችና ለዜጎች አስፈላጊ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ መርሐ ግብሮችን በመተግበር ያደረጉትን ጥረት ያገናዘበ መሆኑም ተገልጿል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁለንተናዊ ዕድገትን በማጠናከር፣ አገልግሎቶችን በፍትሐዊነት በማዳረስ እንዲሁም በከተማዋ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ቅድሚያ በመስጠት ረገድ ያሳዩት አመራር ለስኬታቸው ቁልፍ ሚና እንደነበረውም ተመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ዘላቂ፣ ለአካባቢ ተስማሚ፣ በቴክኖሎጂ የተመራ እና ሁለንተናዊ የከተማ ገፅታ በመገንባት ላይ ያተኮረው የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ‘በቴክ-ኢንኖቫ ሲቲ’ ምድብ ለግማሽ ፍፃሜ ያበቃቸው የከተማዋን መጠነ ሰፊ የልማት ዕድገት ይበልጥ ማሳያ ሆኗል።

ከንቲባ አዳነች በአካል በዝግጅቱ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው ለድርጅት ኮሚቴው በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ይህ እውቅና የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት ለማሻሻል ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን በመሰዋት የጋራ ጥረት ያደረጉ አካላት ሁሉ ውጤት ነው” ብለዋል።

እንደነዚህ ያሉ መድረኮች ለመሪዎች የተሻሉ ልምዶችን እንዲለዋወጡ እና ይበልጥ እንዲበረቱ ተጨማሪ አቅም እና ተነሳሽነት ይፈጥራልም፤  “ይሄ ጅማሮ ነው፤ ተባብረን ገና ብዙ እንሠራለን” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) “ሽልማቱ አዲስ አበባ ከጥቂት አመታት በኋላ ሌሎች ከተሞች የደረሱበትን አልፋ እንደምትሄድ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡

ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ስማርት ሲቲ የሚለው ሀሳብ ስልጡን ከተሞችን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በ2025 ድጂታል ትሆናለች የሚል ስትራቴጂ ተቀምጦ እየተሰራ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ አዲስ አበባ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ አንፃር ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኮሪደር ልማቱን በዋናነት ጠቅሰዋል፡፡

ስልጡን ከተሞችን ለመፍጠር ከተማ መጀመሪያ መልማት አለበት ያሉት ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማቱ ደግሞ ለዚህ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ አመራሩ በቁርጠኝነት ስማርት ከተማን ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ዘላቂ የስራ ዕድል እንዲፈጠር፣ በእጅ አሊያም በተለምዷዊ አሰራር የሚከናወነው ነገር ቀርቶ በቴክኖሎጂ በተለይም ወረቀት አልባ አሰራርን ለመፍጠር ለአብነትም በመሬት አስተዳደር፣ በትራንስፖርት ሲስተም፣ መናፈሻ ስፍራዎች፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በሲሲ ቲቪ ካሜራ ወንጀለኛን ለመከላከል  በጥቅሉ በጣም ግልፅ የሆነች ከተማ ለመፍጠር እና በአለም አቀፍ ደረጃም የስማርት ዲፕሎማሲ፣ ቱሪዝም እና ከዘላቂ ልማት ጋር ተያይዞ አሸናፊ እንድትሆን የከተማዋ አመራር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ስማርት ከተማን ከመፍጠር አንፃር በደቡብ ኮሪያ በተደረገው አለም አቀፍ ውድድር አዲስ አበባ መመረጧ በጣም ትክክል ነው፡፡ ይህም ብዙ ቴክኖሎጂ አለን ሳይሆን ህዝብን በዘመናዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር ምን ያህል ቴክኖሎጂን ተጠቀሙ የሚለው ነው ዋና መለኪያው፡፡ በዚህም ከከተማዋ ልማት ህዝቡ የተጠቀመው ታይቶ ለአብነትም፣ በቤት ልማት፣ በትራንስፖርት ስርዓት፣ በመናፈሻ ስፍራዎች እና መሰል ነገሮች አዲስ አበባ ተመራጭ እየሆነች ነው፡፡ በአጠቃላይ በደቡብ ኮሪያ የተገኘው አለም አቀፍ ሽልማት አዲስ አበባ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከተለቻቸው ስልቶች ውጤት ነው።

በተለይም በኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ በማታ ምን እንደምትመስል አለም እያየ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ አዲስ አበባ በዘመናዊ መንገድ በአለም ተመራጭ ከተሞች ቋት ውስጥ እየገባች ነው፡፡ በመሆኑም ንፁህና ውበት ያለው ከተማ ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ያሉ አመራሮች ስለሆኑ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ72 አገሮችና 115 አቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች መካከል በስማርት ሲቲ ንቅናቄ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ከንቲባዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ኤክስፐርቶችን በመለየት እውቅና የሚሰጠውን የሴኡል ስማርት ሲቲ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ተገቢ ነው ብለዋል ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፡፡

ሽልማቱ አዲስ አበባ ከጥቂት አመታት በኋላ ሌሎች ከተሞች የደረሱበትን አልፋ እንደምትሄድ ማሳያ ነው ያሉት ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ አየር ንብረት በአጠቃላይ በተፈጥሮ ያላት ፀጋ እጅግ በጣም ተስማሚ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገብ የምትችል ከተማ ናት፡፡ ለዚህም በኮሪደር ልማቱ የመጡ ለውጦችን ለአብነት ማንሳት እንደሚቻልም ጠቅሰዋል፡፡

ከተማዋ በዚሁ ከቀጠለች፣ የገበያ፣ የቱሪዝም፣ የልማት፣ አሁን ካለችበት በላይ የበለጠ የዲፕሎማቲክ ማዕከል ትሆናለች። አሁን ለመዲናዋ የበለጠ አስደናቂ ጊዜ እየመጣ ነው። ሽልማቱም የዚህ ማሳያ ነው። ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከዚህ በፊትም በርካታ ሽልማቶችን ማግኘታቸውን ያወሱት ምሁሩ፣ አመራሩ እንደ ሻማ እየቀለጠ ለህዝቡ ብርሃንን የሚሰጥ ነው። ከተማን መምራት ደግሞ ቀላል አይደለም። በመሆኑም እራስን መስጠት ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በመዲናዋ እየመጡ ያሉ ልማቶች በቀላሉ አልተመዘገቡም፤ ይልቅ በአመራሩ የቅርብ ክትትልና ቁርጠኝነት የመጡ ናቸው፡፡ ሽልማቶቹም የዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሽልማቶች ደግሞ ለከተማዋ ብዙ ዕድሎችን ያስገኙላታል፡፡ ለአብነትም፣ ባለሀብቶች፣ ባለሙያዎች፣ ነዋሪዎች፣ አመራሮችን በማገዝ የበለጠ ከተማዋ እንድትለማ የሚያነሳሳ እና ይህንን ልማት የሚተባበር አዲስ አበቤን የምንፈጥርበት ነውም ብለዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለያዩ ጊዜያት አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ለአብነትም ባሳለፍነው አመት አሜሪካ ጆርጂያ ግዛት ከሚገኘው ትሪኒቲ ኢንተርናሽናል አምባሳደርስ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እና የጆርጂያ ግዛት የክብር ዜግነት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የትሪኒቲ ኢንተርናሽናል አምባሳደርስ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ዶ/ር ዣክሊን ሞሀየር ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ለሕዝብ ተጠቃሚነት እና ለሰላም ላበረከቱት ታላቅ አስተዋፅዖ፣ ያሳዩት በሳል እና ምሳሌያዊ አመራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ መሪዎች ምሳሌ የሚሆንና መነሳሳት የሚፈጥር በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ይህንን (Doctorate of Philosophy) እንዳበረከተላቸው ገልፀዋል::

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለመቀየር እና የነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ለሌሎች ሃገራት መሪዎች አርአያ የሚሆን ስራ በመስራታቸው የጆርጂያ ግዛት የክብር ዜግነት ሽልማት እንደተበረከተላቸው የግዛቱ ሴናተር ጋይል ዴቨንፓርት በመድረኩ ላይ ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዚህ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋና ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡

ባሳለፍነው ዓመት የአፍሪካ ወጣት አመራሮች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ መከናወኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ መድረክ ከንቲባዋ በከተማቸው ባሳዩት በሳልና ምሳሌያዊ አመራር እውቅና እና ሽልማት ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩልም ከንቲባ አዳነች አቤቤ መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው እና በየዓመቱ በአፍሪካ ምርጥ ብቃት ያሳዩ አፍሪካውያን መሪዎችን የሚሸልመው የአፍሪካ ሊደርሺፕ መጽሄት የሚያዘጋጀው የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ መሪ (African leadership magazine person of the year) የ2016 ዓመተ ምህረት ሽልማትም አሸናፊ ሆነዋል፡፡

ከንቲባዋ የተሸለሙት፣ ሙስናን በመዋጋት፣ ተቋማዊ ሪፎርሞችን በመተግበር፣ መልካም አስተዳደር በማስፈን፣ በአመራር ብስለት እንዲሁም ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ ባሳዩት ውጤታማ ስራ እንደሆነም በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

በወቅቱ ከቀድሞ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጃካያ ኪኪዌቴ እጅ ሽልማቱን የተቀበሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ስለተበረከተላቸው ሽልማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ “የማይበገር የአፍሪካ ኢኮኖሚ መገንባት” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የሽልማት መርሃ ግብር ላይ ዘጠኝ ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካዊያን መሪዎች ተሸላሚ መሆናቸው መገለፁ አይዘነጋም።

የሴኡል የሜትሮፖሊታን መንግስት በይፋዊ ገፀ ድሩ ባሰፈረው መረጃ መሰረት፣  የ“ሴኡል ስማርት ከተማ 2024” ተነሳሽነት ቴክኖሎጂን፣ ዘላቂነትን እና የዜጎችን ተሳትፎ የሚያዋህድ አዲስ የከተማ አካባቢ ለመፍጠር ጉልህ እርምጃን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የዚሁ ጅምር አካል “የስልጡን (ስማርት) ከተማ ባለ ራዕይ መሪ ሽልማት” የተቋቋመው በስማርት ከተማ መፍትሄዎች፣ ልማትና ትግበራ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች እውቅና ለመስጠት ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ከተማዋ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳን ተቀብላ፣ እንደ አይኦቲ፣ ትልቅ ዳታ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ያሉ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን የከተማ ኑሮ ለማሻሻል እየተጠቀመች ነው። ሽልማቱ የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶችን፣ ቀልጣፋ የህዝብ አገልግሎቶችን እና ዘላቂ የከተማ ልማትን በማስፈን የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት ለማሳደግ ከስማርት ከተማ 2024 ኢኒሼቲቭ ጋር በጥምረት ስለመጀመሩም በመረጃው ተመላክቷል፡፡

ይህ ሽልማት በከተሞች መካከል የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር እያስቻለ ሲሆን፣  ይሄውም ሽልማቱ ምርጥ ተሞክሮዎችን በዓለም ዙሪያ ያሉ ከተሞች የሚለዋወጡበት መድረክን አመቻችቷል፤ ለከተማ ተግዳሮቶች የትብብር መፍትሄዎችንም አምጥቷል፡፡ ሽልማቱ በ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘላቂ የከተማ አካባቢዎችን ለመገንባት አስፈላጊ የሆነውን የትብብር መንፈስ እና ፈጠራን ያካትታል ይላል የሴኡል የሜትሮፖሊታን መንግስት በይፋዊ  ገፀ ድሩ ይፋ ያደረገው መረጃ።

መለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review