በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቀጥል ከሁሉም ኃይሎች ጋር ንግግር እየተደረገ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቀጥል ከሁሉም ኃይሎች ጋር ንግግር እየተደረገ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም

በትግራይ ክልል ህግ በማሻሻል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቀጥል ከሁሉም ኃይሎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራርያ ፤ስምምነቱ ታሪካዊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለብዙዎች ልምድ የሚሰጥ ነው ያሉት የፕሪቶሪያው ስምምነት መንግስት ለሰላም ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ያሳየበት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ በውጊያው ምክንያት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዳልቻለ በማስታወስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የሚጠበቁ በበቂ የልተፈጸሙ ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነትም የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን አንስተዋል፡፡ይህ አለመፈጸሙም በዋናነት የትግራይን ህዝብ የሚጎዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም በሰጡት ምላሽ፤ በራያና በጸለምት ጥሩ ስራ መሰራቱን እና ወልቃይት አካባቢ የተጀመሩ ጉዳዮች በተፈለገው ደረጃ አልሄዱም ብለዋል፡፡

መንግስት በማንኛውም ሰዓት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በተፈናቀሉ ዜጎች ላይ የሚሰራው የፖለቲካ ስራ ጉዳት እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰዎችን ችግር ከፖለቲካ መነጠል አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ባለፉት 2 ዓመታት በአቶ ጌታቸው ረዳ ፕሬዝደንትነት እና በታደሰ ወረደ እና ጻድቃን ገ/ተንሳይ ምክትል ፕሬዝደንትነት እየተመራ ያለው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተጨማሪ ጦርነት እንደይፈጠር መስራቱን በማስታወስ ለዚህም አድናቆት እና ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የ2 ዓመታት የአስተዳደሩ ጊዜ በመጠናቀቁም የህግ ማሻሻያ በማድረግ አስተዳደሩ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ ስራውን እየሰራ ህዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀትና የስልጣን ባለቤት የማድረግ ሂደት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

ይህንን ለማድረግም ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሁሉም አካላት ጋር ንግግር ሲደረግ መቆየቱን እና በንግግሩ መሰረት ህግ በማሻሻል ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ያለፉ ስራዎች ተገምግመው በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ሊካሄድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የሚቋቋመው መንግስት በሚቀጥሉት ጊዜያት ለህዝብ እንደሚገለጽም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታውቀዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review