AMN – ታኅሳስ 30/2017
በቻይና ምዕራባዊ ክፍል በሬክተር ስኬል 7.1 የተመዘገበ እና ቲቤት ግዛት የደረሰ ከባድ ርዕደ መሬት ባስከተለው ጉዳት የ126 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ከ14 ሺህ በላይ የነብስ አድን ሠራተኞች ፍለጋ መቀጠላቸው ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ የመንግስት ሚዲያ እንደዘገበው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ያወደመው አደጋ ከደረሰበት ከትናንትናው ዕለት አንስቶ እስከ አሁን ከ4 መቶ በላይ ሰዎችን ማትረፍ ተችሏል፡፡
የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዣንግ ጉኪንግ አደጋው በደረሰበት ሥፍራ በመገኘት እየተሰራ ያለውን የነብስ አድን ሥራ ተመልክተዋል፡፡
በአካባቢው የርዕደ መሬት ክስተት የተለመደ ቢሆንም፣ ይህኛው ግን በቻይና በቅርብ ከተከሰቱ አደጋዎች አስከፊው መሆኑ ተነግሯል፡፡
በሬክተር ስኬል 7.1 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት ንዝረት 10ኪሎ ሜትር ጥልቀት እና በአጎራባች ኔፓል እና ከፊል ህንድ ድረስ እንደተሰማ የአሜሪካ ሥነ-ምድር ጥናት መረጃ ያመላክታል፡፡
አየር ኃይል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከአደጋው የተረፉትን እና በአደጋው ተጎጂ የሆኑ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ሥፍራ ለማዛወር ሥራዎች እየሰሩ መሆናቸውን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሀገር ውስጥ የመንግስት ሚዲያ እንደዘገበው በአካባቢው እስከ አሁን ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሌላ ሥፍራ ተዛውረዋል፡፡
በኢትዮጵያም ከቅርብ ወራት ወዲህ በአፋር፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አከካባቢዎች በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት እየተስተዋለ እንደሆነና ንዝረቱም እስከ አዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ድረስ እየተሰማ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ክስተቱን ተከትሎም መንግስት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ከአካባቢው ወደ ሌላ ሥፍራ የማዛወር ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ እና ባለሙያዎችም አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ እየሰጡ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው፡፡