AMN-ጥር 1/2017 ዓ.ም
በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ዋጋን መሰረት ያደረገ መሆኑን የነዳጅና ኤነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስርዓት አዋጅን አስመልክቶ ከንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል።
አዋጁ በነዳጅ ውጤቶች ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና ግብይቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
የነዳጅና ኤነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ፤ የአዋጁን ጠቀሜታና አስፈላጊነት በተመለከተ ለምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋን መሰረት ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የዓለም የነዳጅ ዋጋ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተረጋጋ የሚባል ስለነበር በኢትዮጵያም የመንግስት ድጎማ እንዳለ ሆኖ ብዙም የዋጋ ማሻሻያ ሳይደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የነዳጅ ማደያዎችን ስማርት በማድረግ የሳተላይት የቁጥጥር ሂደት የመጀመር እቅድ መያዙን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ አጠቃላይ የነዳጅ ስርጭትና ቁጥጥሩን ቀልጣፋና ዘመናዊ የማድረግ ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የተደረገው የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ማሻሻያ የከፋ የኢኮኖሚ ጉዳት እንዳያስከትል በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የነዳጅ ምርቶች ላይ ይደረግ የነበረውን ጥቅል ድጎማ ወደ ታለመለት ደጎማ በመቀየር ከዓለም የነዳጅ መግዣ ዋጋ በታች እየተሸጠ መሆኑን አንስተዋል።
የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስርዓት አዋጅ የነዳጅ ግብይቱን በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በመደገፍ ህገ-ወጥ ተግባራትን መቆጣጠርና የተጠያቂነት አሰራሮችን መዘርጋት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
ከነዳጅ ማደያ ግንባታ፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ከቁጥጥር ስርዓት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችም ዋና ዳይሬክተሯ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አዋጁ ከነዳጅ ማስመጣት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ግልፅ አሰራር የሚፈጥር ስለመሆኑም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምክር ቤቱ የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ስርዓትን ለመደንገግ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በሁለት ተቃውሞ በአንድ ድምፀ ታቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።