AMN- መስከረም 7/2017 ዓ.ም
በምስራቅ አርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ ወላአርባ ቀበሌ የደቡብ ዕዝ ነበልባል ክፍለጦር አባላት በተሰማሩበት የግዳጅ ቀጠና ሲንቀሳቀስ የነበረውን እና የህዝብ ንብረት በመዝረፋ፣ ንፁሃንን በመግደል ፣ በማገትና የአካባቢውን ህዝብ ሲያፈናቅል የቆየውን ጠላት መደምሰሱን የክፍለጦሩ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ለታ አንበሴ ገልፀዋል።
በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ በተወሰደው እርምጃ ጠላት ከፍተኛ ሰበአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደደረሰበት እና በርካታ የጠላት ሃይል እንደተደመሰሰ ተመላክቷል፡፡
7 ምርኮኛ፣450 የክላሽ ጥይት፣ 100 የብሬን ጥይት ከነሸንሸሉ፣ 03 ክላሽ መማረክ መቻሉም ተገልጿል።
በተያያዘ የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ክፍለጦር ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር አውሏል።
በሰሜን ወሎ የሚገኘው የሰሜን ምስራቅ ዕዝ መተማ ክፍለ ጦር በፀሀይ መውጫ ፣ በዳውንትና ፣ መቄት ወረዳዎች ባደረገው የተጠናከረ ክትትል ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክፍለጦሩ ምክትል አዛዥ ለውጊያ አገልግሎት ሌተናል ኮሎኔል ጌታሁን ማሞ ተናግረዋል።
ክፍለጦሩ በወሰደው እርምጃ 12 ክላሽ ፣ 1 ኋላቀር መሣሪያ ፣ እንዲሁም ትጥቆችን በንቃት ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ምክትል አዛዡ መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።