በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከእሲያ የመሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኩን ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ የተካሔደው ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ የእኤአ 2025 የጸደይ ስብሰባ ጎን ለጎን ነው።
በውይይቱ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ኢትዮጵያን በመጎብኘታቸውና በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታ ዕቅድና ሌሎች ዘርፎችን ለመደገፍ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
የእሲያ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኩን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው ግዙፍ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም እና ለውጥ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ባንኩ ኢትዮጵያ ምርታማነትን በሚያሳድጉ፣ የስራ ዕድል በሚፈጥሩ፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን በሚያሳድጉና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በሚያበረታቱ ተግባራት ላይ በምታከናውናቸውና ለመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
ሁለቱ ወገኖች ትብብራቸውን ለማጠናከር የተስማሙ ሲሆን በተለይም ቀጣናውን በትራንስፖርትና በመሰረተ ልማት ለማገናኘት በሚደረገው ጥረት የባንኩ ድጋፍ የባንኩ ድጋፍ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይም መምከራቸውን ኢዜአ ገንዘብ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡