በአንድ ወር ውስጥ ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ በተካሄደ ቁጥጥር ከ1 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

You are currently viewing በአንድ ወር ውስጥ ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ በተካሄደ ቁጥጥር ከ1 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

AMN – ታኅሣሥ -3/2017 ዓ.ም

በአንድ ወር ውስጥ በተካሄደ የኦፕሬሽን ስራዎች ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ 1 ሺህ 145 የሚሆኑ ነጋዴና ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ቢሮው አስታወቀ

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የህግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ እንደገለፁት በተቀናጀ መልኩ ከህዳር ወር ጀምሮ በተሻለ ንቅናቄ ሲሰራ የነበረው የደረሰኝ ቁጥጥ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል ።

በመርካቶ እና በሌሎች ዋና ዋና የግብይት ቦታዎች ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው በከተማዋ 40 ሺህ 153 የሚሆኑ የንግድ ድርጅቶችን በአንድ ወር ውስጥ ጉብኝት ለማድረግ መቻሉን ገልፀዋል ።

ትልልቅ ግብይት ይኖርባቸዋል ተብለው በተለዩ በ8 ቅርንጫፍ ማዕከላት እንዲሁም ቁጥጥር ሊደረግ በሚገባቸው 3 የመርካቶ ቅርንጫፎች በአስመጪ ፣ በአከፋፋይ ፣ በአምራችና ቸርቻሪዎች ላይ ከደረሰኝና ከማሽን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በትኩረት መሠራቱን ገልፀዋል ።

በዚህ በአንድ ወር ውስጥ በተካሄደው የኦፕሬሽንና የተቀናጀ የቁጥጥር ስራ 1145 የሚሆኑ ድርጅቶች ላይ ርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል ።

ከዚህ ውስጥ 826 ግብር ከፋዮች ደረሰኝ ባለመቂረጥ ቀሪዎቹ 319 የሚሆኑት ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ ሌሎች ጥፋቶች ውስጥ በመገኘታቸው በድምሩ 1 ሺህ 145 የሚሆኑ ነጋዴዎች ከደረሰኝ ግብይት ጋር በተያያዘ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል ።

ደረሰኝ የመቁረጥ እንቅስቃሴው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱንና ደረሰኝ የሚጠይቅ ነጋዴም መኖሩ የገለፁት ሀላፊው ይህ ተግባር በበለጠ ስራ የሚጠይቅና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ማሳወቃቸውን ከቢሮው ያገነነው መረጃ ያመለክታል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review